የተሰጠው ስልጠና በዘርፉ ያላቸውን ግንዛቤ የሚያሳድግላቸው መሆኑን በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና የወሰዱ የትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ደኅንነት ባለሙያዎች ገለጹ

የተሰጠው ስልጠና በዘርፉ ያላቸውን ግንዛቤ የሚያሳድግላቸው መሆኑን በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና የወሰዱ የትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ደኅንነት ባለሙያዎች ገለጹ

“የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመከላከልና የትራንስፖርት አሰጣጥ ችግሮችን ለማሻሻል የባለድርሻ አካላት ሚና” በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ከካፋ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ የትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎች፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ የትራፊክ ፖሊሶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ የወጣውን ህግ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የጀመረውን መልካም ተግባር አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

የቀረቡ የስልጠና ሰነዶች ከዚህ በፊት የነበረንን እውቀት የሚያሳድጉና በቀጣይ ለሥራ የሚያነሳሱ ናቸው ብለዋል፡፡

አዲሱን ደንብ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ውስንነቶች እንደሚታዩም ገልጸዋል፡፡

መናኸሪያዎች አካባቢ ከስምሪት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ጉድለቶች ሊቀረፉ እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተለይ ከትርፍ መጫንና ታሪፍ ጋር ተያይዞ አሁንም ችግሮች መቀጠላቸውን አንስተው፤ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በሁሉም አካላት ዘንድ ወጥ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

መምሪያው ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተባብሮ ስልጠናውን ማዘጋጀቱ ያስመሰግነዋል ያሉት የካፋ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኢ/ር አጥናፉ አባተ፤ አዲሱ 557 ደንብ እያመጣቸው ያሉ ለውጦችን በመለየት በቀጣይ ክፍተት ባለባቸው ላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ደንብ የሚተላለፉ አካላትን ከመቅጣት ይልቅ ማስተማር ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸው፤ የትራንስፖርት ዘርፍ ባለሙያዎችና የትራፊክ ፖሊሶች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የካፋ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመዴ አንዳርጌ፤ የትራፊክ ፖሊሶች ከስልጠናው ማግስት የማህበረሰቡን ቅሬታ መፍታት የሚያስችል ተግባር መከወን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በተለይ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አንዳለበት አመላክተዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ከመከላከልና ተከታትሎ እርምጃ ከመውሰድ አንፃር ጉድለቶች መኖራቸውን አንስተው፤ አስተማሪ ርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የፍጥነት መቆጣሪያዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ዘመዴ፤ በአጠቃላይ የህዝቡን ፍላጎት የሚያረኩ ሥራዎችን መሥራት በቀጣይ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተሰጠው ስልጠና ተጨማሪ ልምድና እውቀት ያስገኘ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘመዴ፤ ለዩኒቨርሲቲው ያላቸውን ምስጋናም አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ዳንኤል መኩሪያ – ከቦንጋ ጣቢያችን