ሀዋሳ፡ ግንቦት 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማህበራዊ ዘርፎች ላይ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማጎልበት ባሻገር ትውልድ ተሻጋሪ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዶ አህመድ አስታወቁ።
የቡታጅራ ከተማ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ለማከናወን የዲዛይን እና የመሬት ዝግጅት ስራ ስለመጠናቀቁም ተገልጿል።
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ምስራቅ ጉራጌ ዞን የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከኢኮኖሚው ባሻገር በማህበራዊ ዘርፍም አመርቂ ተግበራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዶ አህመድ እንዳሉት፤ በከተማ አስተዳደሩ በርካታ ማህበረሰባዊ ጠቀሜታ የላቸው ተግበራት እየተከናወኑ ነው።
ከተግባራቱም የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ቀዳሚ ነው ያሉት ከንቲባው፤ ይህም ነገን ታሳቢ ያደረገ፣ ትውልድን የሚያንጽ ትልቅ ተቋም ነው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ልማቱ ላይ ቀደምት ታሪክ ያለው ቢሆንም መሰል ትላልቅ ተቋማት ከመገንባት አንጻር ውስንነት ያለ በመሆኑ የማህበረሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አውስተው፤ ግንባታው ለጥያቄው መልስ የሰጠ በዘርፉ የሚታየው የጥራት ችግርም የሚቀርፍ መሆኑንም ከንቲባው ገልጸዋል።
አሁን ላይ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታን ለማከናወን የ3.2 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንና የማህበረሰቡን ማንነት አጉልቶ በሚያሳይ እና ሁሉን አቀፍ አገልግሎት መስጠት በሚችል መልኩ የግንባታ ዲዛይን ተዘጋጅቶ መጠናቀቁንም አመላክተዋል።
በመጀመሪያ ዙር ከ7 መቶ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር አቅም እንዳለው የተነገረው ይህ ተቋም፤ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ ባለፈ ተማሪዎች በአለም ብሎም በሃገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት ከንቲባው።
በማህበረሰብ ተሳትፎ እና በውስጥ አቅም የሚገነባው የአዳሪ ትምህርት ቤት በዚህ ወቅት ግንባታውን ማስጀመር የሚያስችል በጀት እንደተዘጋጀ ተናግረው፤ ህብረተሰቡ በተለይም ባለሃብቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ሌላኛው በማህበራዊ ዘርፍ ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የህዝብ መድሃኒት ቤት ለመክፈት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንና ይህም ማህበረሰቡን የሚጠቅም ነው ብለዋል።
የመድሃኒት መወደድና እጥረት ከኑሮው ጫና ጋር ተዳምሮ ህብረተሰቡ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጥ የሚያደረገውና በመንግስት ኢኒሼቲቭ እየተገነባ የሚገኘው የህዝብ መድሃኒት ቤቱ ግንባታው ተጠናቆ በቀጣይ ወራት ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ነው ያሉት ከንቲባው።
በመሆኑም በማህበራዊ ዘርፎች ላይ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማጎልበት ባሻገር ትውልድ ተሻጋሪ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት አቶ አብዶ፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ልማት ወዳዱ የከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰብ በከተማው በሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ተግባራት የሚያሳየው ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ይበልጥ በማላቅ በተለይም ትውልድ ተሻጋሪውን የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ በተያዘው ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ከንቲባው መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በቅርቡ በሚሰጠው የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተና ላይ ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ትምህርት መመሪያ አስታወቀ
“የብልጽግና ጉዞአችንና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ክልላዊ የንግዱ ማሕበረሰብ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው
በዞኑ ኩረጃን የሚፀየፍ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ