ሀዋሳ፡ ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡና አልሚ ባለሀብቶችና አቅራቢ ነጋዴዎች ቡናን በጥራትና በብዛት በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የካፋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
የካፋ ዞን ቡና አዘጋጆች እና አቅራቢዎች ማህበር 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፥ ቡና አልሚ ባለሀብቶችና አቅራቢ ነጋዴዎች ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ማህበሩ የቡና ግብይት ስርዓቱ ቀልጣፋና ምቹ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ያበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ጠቁመው፥ ለውጤታማነቱ ሁሉም አካላት ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
ማህበሩ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም በስራ እድል ፈጠራ፣ የዞኑን የገቢ አቅም ከማሳደግና የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንፃር ያከናወናቸው ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የምርታማነት እና የጥራት ችግር እንዲሁም ከግብይት ስርዓቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ማህበሩ ሊፈታ እንደሚገባው አቶ እንዳሻው አስገዝበዋል።
ቡና የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ ከመሆኑም ባሻገር ሀገሪቱ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ቀዳሚዉን ስፍራ የሚይዝ በመሆኑ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል ያሉት ደግሞ በካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሞገስ ተክሌ ናቸዉ።
በዞኑ 219 ሺህ 22 ሄክታር መሬት በቡና የተሸፈነ ሲሆን 124 የእሼት ቡና መፈልፈያና 78 የደረቅ ቡና መቀሸሪያ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ጠቁመው፥ በዞኑ 113 አልሚ ባለሀብቶች እና 250 ቡና አቅራቢ ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ህብረቱ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ማለትም የሠራተኞች ጉልበት ብዝበዛ፣ በተልይም አቅመ ደካሞችና ህፃናት ላይ የሚፈፀም የጉልበት ብዝበዛ፣ የሠራተኞች ደመወዝ እና መጠለያ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ሞገስ አሳስበዋል።
ህገወጥ የቡና ግብይትን ለመከላከል ሁሉም አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ማህበሩ በ2015 ዓ/ም ተቋቁሞ ወደስራ መግባቱንና የማህበሩ መቋቋም ለብዙዎች ስራ የፈጠረና አምራችና አቅራቢ ነጋዴዎችን ከተለያዩ እንግልቶች መታደግ የቻለ መሆኑን የገልጹት የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ለማ ማሞ ናቸው።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ወንድሙ ወ/ሚካኤልና አቶ አስማማው ወ/ማሪያም የቡና ጥራት ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሠሩና ህብረቱ ያወጣቸውን ህጎች እንደሚተገብሩ ተናግረዋል።
በተለይ ደግሞ ህገወጥ የቡና ግብይት እንዲቆም የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ በማርታ ታምሩ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ መቆርቆር ቀበሌ ያስገነባው የንጹህ መጠ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የኡዱሂያ የዕርድ ስርዓት….የአብሮነት ነፀብራቅ
በቅርቡ በሚሰጠው የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተና ላይ ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ትምህርት መመሪያ አስታወቀ