ዉብ እና ፅዱ አካባቢን በመፍጠር ሕብረተሰቡን ከበሽታ ለመጠበቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረዉ መቀጠል እንዳለባቸዉ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዉብ እና ፅዱ አካባቢን በመፍጠር ሕብረተሰቡን ከበሽታ ለመጠበቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረዉ መቀጠል እንዳለባቸዉ የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለጹ።
በልዩ ወረዳዉ የቆላ ከባዳ ቀበሌን ፅዱ መንደር እና ጎዳና በማድረግ የምረቃ ፕሮግራም በዛሬዉ እለት ተከናዉኗል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት በልዩ ወረዳዉ በሁሉም ቀበሌያት አከባቢዉን ዉብ እና ፅዱ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸዉን ገልፀዋል።
በዛሬዉ እለት ለምርቃት የበቃዉ የቆላከባዳ ቀበሌ የዚሁ አንድ አካል መሆኑን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው ዉብ እና ፅዱ አካባቢን በመፍጠር ሕብረተሰቡን ከበሽታ ለመጠበቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረዉ መቀጠል እንዳለበት አመላክተው አከባቢን ፅዱ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸዉን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
ህብረተሰቡ አከባቢዉን ፅዱና ዉብ በማድረግ ቀዳሚ እንደሆነ ሁለ የአከባቢዉን ሰላምና ደህንነት ዘላቂ በማድረግ ልማታዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ መቻል እንዳለበት አክለዋል።
የልዩ ወረዳዉ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልኸይ ኑርሀሰን በበኩላቸዉ መንግስት የህብረተሰቡን ጤና በማስጠበቅ አምራች ዜጋን ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ተላላፊ በሽታዎችን ለመካላከል አከባቢን ማስዋብ ዋና ተግባር መሆኑን ሀላፊዉ በመግለፅ በልዩ ወረዳዉ ባለፈዉ በጀት አመት ጀምሮ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
በልዩ ወረዳዉ እየተሰራ ባለዉ ስራ ዉጤታማ መሆኑን ያነሱት ሀላፊዉ ዛሬ ለምርቃት የበቃዉ የቆላከባዳ ቀበሌን ጨምሮ 11 ቀበሌያት ተግባራዊ መደረጉንና በቀጣይ ጊዜያት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ ከጤና ኤክስቴንሽን የሚሰጠዉን ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ አከባቢዉን ፅዱ በማድረግ ከበሽታዎች እራሱን መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ወ/ሮ ዙልፋ ሰዒድ በቀቤና ልዩ ወረዳ የቆላከባዳ ቀበሌ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ሲሆኑ ቀበሌዉን ዉብ እና ማራኪ በማድረግ ሞዴል ማስደረጋቸዉን በመግለፅ ህብረተሰቡ አከባቢዉን እንዲጠብቅ፣ መፀዳጃ ቤት በአግባቡ እንዲጠቀም ድጋፋቸዉን አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ቀበሌያቸዉ ፅዱ ሆኖ መመረቁ ከበሽታ እራሳቸዉን ለመከላከል ያለዉ ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንን ለማጠናከር የተለያዩ አደረጃጀቶችን ተጠቅመዉ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሳውላ ካምፓስ ለ9ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎችን አስመረቀ
ዲግሪው “ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ተስፋና የትውልድ ኃላፊነት ነው” – አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)
በክልሉ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ