የ2019 የትምህርት ዘመን ምዝገባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የ2019 የትምህርት ዘመን ምዝገባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
በዞኑ ከ286 ሺ በላይ ተማሪዎች በመደበኛ እና ቅድመ መደበኛ ለመመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱ ተጠቁሟል፡፡
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም የምዝገባ አጀማመር አስመለክቶ ባደረጉት ምልከታ እንደገለፁት፥ የ2019 የትምህርት ዘመን ምዝገባ በዞኑ በሁሉም ትምህርት ቤቶች መካሄድ መጀመሩን ገልጸዋል።
በዞኑ በቅድመ መደበኛ ከ61ሺ እና በመደበኛ ደግሞ ከ225 ሺ በላይ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የምዝገባ ሂደቱ በጊዜ መጀመሩ በዞኑ በትምህርት አጀማመር ወቅት የሚፈጠረው የትምህርት ብክነትን ለመከላከል እንደሆነ ጠቁመው፥ ለተማሪዎች የመማሪያ አካባቢዎችን ምቹ በማድረግ አስፈላጊውን ትምህርት እንዲያገኙ ትምህርት ቤቶችን የመጠገን፣ ወንበር፣ ጥቁር ሰሌዳና ሌሎችም የትምህርት ቁሳቁሶች የማሟላት ስራ መስራቱን አቶ መብራቴ ጨምረው ተናግረዋል።
የትምህርት አመራሮች እና ሱፐርቫይዘሮች በክረምት ወራት የትምህርት ቤቶች የቅደመ ዝግጅት ተግባራት ሲያከናውኑ መቆየቱን የጠቆሙት ኃላፊው፥ የምዝገባ ሂደቱን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲጠናቀቅ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
በትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ መሰረት ዜጎች በነፃ ትምህርት ማግኘት እንዳለባቸው መወሰኑን የተናገሩት ኃላፊው፥ ለዚህም እንደ ጉራጌ ዞን ከቅድመ አንደኛ ክፍል ጀምሮ በየትኛውም አካባቢ ለምዝገባ የሚባል ክፍያ እንደማይጠየቁ ጠቁመዋል።
የትምህርት ስራ በደቂቃና በክፍለ ጊዜ የተሸነሸነ መሆኑን ያወሱት አቶ መብራቴ፥ ለዚህም ተማሪዎች በጊዜ ተመዝግበው ከመስከረም 5/2019 ዓ/ም ጀምሮ በትምህርት ገበታቸው ላይ ለመገኘት ዝግጅት እንዲያደርጉ ጠቁመው፥ ወላጆች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን ሲያስመዘግቡ አግኝተን ያነጋገርናቸው ከተማሪ ወላጆች መካከል አቶ ዘይኑ መሃመድ እና ወይዘሮ አልፍያ ሙዘሚል በሰጡት አስተያየት፥ ያለ እንግልት በተሳካ ሁኔታ ልጆቻቸው እንዳስመዘገቡ ጠቅሰው፥ ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት እንዲጀምሩ የትምህርት ቁሳቁስ ከማሟላት ጀምሮ አስፈላጊው ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ተማሪ አብድል ሰላም ዘይኑ እና ቤልቸሬ ታደሰ በሰጡት አስተያየት፥ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ትምህርት ቤት በአካል ተገኝተው መመዝገባቸው እንዳስደሰታቸው እና በትምህርት ዘመኑ የሚረዳቸውን የክረምት ወራት የድጋፍ ትምህርት በመማርና የተለያዩ መፅሃፍት በማንበብ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ዘጋቢ: እርካብነሽ ወልደማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በኮንታ ዞን የሽግግር ም/ቤት 4ኛ ዙር 4ኛ ሥራ ዘመን 26ኛው መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
በክረምት ወራት የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች ወጣቶች አልባሌ ስፍራ እንዳይውሉ ከማድረግ በተጓዳኝ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ እድል እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ
በአርሰናል እንደ አዲስ ብርሃን የፈነጠቀው ክርስቶስ ጾሊስ