የማህበረሰቡን የልማት ተነሳሽነት ሊያካክስ የሚችል የልማት ስራ እየተሰራ ነው – የቡታጅራ ከተማ ከንቲባ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማህበረሰቡን ያለውን የልማት ተነሳሽነት ሊያካክስ የሚችል የልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዶ አህመድ ገለፁ።
በከተማ አስተዳደሩ ደረጃውን የጠበቀ የ25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ እየተፋጠነ ስለመሆኑም ተመላክቷል።
የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆነውና የከተሞች እድገት ከፍ የሚያደርገው የኮሪደር ልማት በሃገሪቱ ደረጃውን ጠብቆ ግንባታ ከሚከወንባቸው ከተሞች አንዱ በምስራቅ ጉራጌ ዞን የሚገኘው የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ነው።
የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዶ አህመድ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በከተማው የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎችም እየተሰሩ ያሉ የመንግስትና የፓርቲ ኢኒሼቲቮች በጥንካሬ የሚገመገሙ ናቸው።
ይህን ኢኒሼቲቭ በደስታ የተቀበለው የከተማው ማህበረሰብ ሽልማት ያለው እስኪመስል ድረስ የኮሪደር ልማት ግንባታ የሚከናወንባቸው ቦታዎች ከይገባኛል ነጻ ማድረጉን የገለጹት ከንቲባው፥ ለዚህ አኩሪ ህዝብ ከምስጋናም በላይ ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነቱን ሊያረጋግጡ የሚችሉ የልማት ስራዎችን በመስራት እንክሰዋለን ነው ያሉት።
ለዚህም የከተማውን የእድገት ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ደረጃውን የጠበቀ የ25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ አጠናቆ ለማስመረቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከ5 መቶ ሚለየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ እየተገነባ የሚገኘው ይህ የኮሪደር ልማት እስካሁን ባለው ሂደት አምስት ሳይቶች ግንባታቸው 90.2 በመቶ መድረሱና ወጪውም 63 ከመቶ መሸፈኑን አንስተዋል።
በአካባቢው ኢንተርፕራይዞች አማካይነት የማህበረሰቡን ባህል በሚገልጽ መልኩ ደረጃውን የጠበቀ እስማርት ፖል በማምረት የሙከራ ተከላ ተደርጓል፤ ግሪነሪውም በተፋጠነ መልኩ እየተሰራ ነው ሲሉ በቆይታችን ወቅት ከንቲባው ተናግረዋል ።
በመሆኑም የኮሪደር ልማቱ የፓርኪንግ፣ የፕላዛ፣ የፋውንቴይን እና ሌሎችም የኮሪደር መሰረታዊያን ያሟላ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመው የሁለቱ ወንዞች ዳርቻ ለማልማት የሚያስችል የዲዛይን ስራ መጠናቀቁም አንሰተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በውስጥ አቅም ከ334 ሚለየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከፈትህ መስጅድ- ጨርቃጨርቅ- ዝዋይ መታጠፊያ የአስፓልት መንገድ ከነ ኮሪደር ልማቱ እየተገነባ ነው ያሉት አቶ አብዶ፥ በከተማው የሚገነባው የ8.7 ኪሎ ሜትር የዋናው መንገድ የደብል ሮድ የአስፓልት ግንባታ ከይገባኛል ነጻ ተደርጎ በቅርቡ ወደ ግንባታ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በመሆኑም አብዛኛው የከተማው ክፍል በአስፓልት መንገድ ለማስተሳሰር ሰፊ ስራ እየተሰራ ከመሆኑም በላይ የከተማውን ደረጃ ከፍ የሚያደርገውን የኮሪደር ስራ በሁሉም አቅጣጫ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ህበረተሰብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ከንቲባው መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ መቆርቆር ቀበሌ ያስገነባው የንጹህ መጠ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የኡዱሂያ የዕርድ ስርዓት….የአብሮነት ነፀብራቅ
በቅርቡ በሚሰጠው የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተና ላይ ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ትምህርት መመሪያ አስታወቀ