ሙያዊ ግዴታና ኃላፊነታችንን በመወጣት ለጥያቄያችን ምላሽ ልንጠብቅ ይገባናል – የቤንች ሸኮ ዞን የጤና ባለሙያዎች
ሀዋሳ፡ ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሙያዊ ግዴታና ኃላፊነታችንን በመወጣት ለጥያቄያችን ምላሽ ልንጠብቅ ይገባናል ሲሉ በቤንች ሸኮ ዞን የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች ገለጹ።
የዞኑ ጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች “የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት ለሀገር ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ በሚዛን አማን ከተማ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን እንደተናገሩት የማንኛውም ሀገር የልማት ምሶሶ የሚቆመው ጤናማና አምራች ዜጋ ሲፈጠር በመሆኑ በዚህ በኩል በመንግስት ትኩርት ተሰጥቶ እየተሰራበት ነው ብለዋል።
ዋና አስተዳሪው አክለውም ጥረቶች ሁሉ በህዝብ ተሳትፎ ካልታገዘ የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ ስለማይችል ውይይት ማድረግ ለጤናማ ማህበረሰብ ግንባታ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።
የውይይቱን ሰነድ ያቀረቡት የዞኑ ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ኤሊያስ ምናሴ ባለፋት ስድስት እና ሰባት አመታት እንደሀገር በጤናው ዘርፍ በርካታ ስራዎች ተሰርተው ውጤት የተገኘባቸው መሆናቸውን ገልፀዋል።
በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ቢገኝባቸውም ችግሮች አልነበሩም ማለት አይደለም ያሉት የመምሪያው ኃላፊ እንደመንግስት ችግሮችን ለመቅረፍ ብዙ እርቀት በመጓዝ መፍታት እንደተቻለና ቀሪዎችንም ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት ባለሙያዎች በሰጧቸው ሀሳቦች እንደ ሀገር በጤና ባለሙያዎች የተነሱ ጥያቄዎች የኛም ጥያቄ ቢሆንም የሙያ ግዴታችንን እና ኃላፊነታችን በመወጣት ነው ለጥያቄያችን ምላሽ የምንጠብቀው ብለዋል።
የህክምና ባለሙያዎቹ አክለውም የደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ያለመከበራቸው እንደ ችግር አንስተዋል።
አንዳንድ ተቋማት ላይ የሚያገኟቸውን አይነት አገልግሎት በራሳቸው ተቋም እንደ ነፃ ህክምና የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።
ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ስለሚሠሩ በጉዳዩ ዙሪያ ትኩረት እንዲሰጥና በሚሠሩባቸው ተቋማትም የግብአት እጥረቶች እንዲሟሉላቸው ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ የዞኑ ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ኤልያስ ምናሴ ባለሙያዎቹ ካነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ በዞን ደረጃ ምላሽ ሰጥተው እንደሚሰሩ አመልክተው ቀሪውን ጥያቄዎች በየደረጃው ላሉ የበላይ አካል እንደሚያቀርቡም ገልፀዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን የጤናውን ዘርፍ የተሻለ ቦታ ለማድረስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አመልክተው ባለሙያዎች የሚያነሱትን ጥያቄ ምላሽ የሚያገኙት የተጣለባቸውን ሙያዊ ግዴታ እየተወጡ መሆን አለብት ብለዋል።
የጤና ባለመያዎቹና ሠራተኞች በዞኑ በፌደራል መንግስት እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀው ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የአካባቢውን ገፅታ ከመለወጣቸው በተጨማሪ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንደሚያደረግ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ አሣሣኸኝ – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል