በኪነጥበብ ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኪነጥበብ ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ።
የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ “ሀገር እና ጥበብ: ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል ዞናዊ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሔዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ የኪነ ጥበብ ስራዎች በሃገር ደረጃና በክልሉ መንግስት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል።
የኪነ ጥበብ ዘርፉ ትኩረት እንዲሰጠውና ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሊያግዝ የሚችል የህግ ማእቀፍ ኖሮት በአግባቡ እንዲመራ መመሪያና ደንብ መዘጋጀቱን ጠቁመው፥ ክልሉ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በክልል እና በዞን ደረጃ የባህል ፌስቲቫል እና ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱን አቶ ደግነህ ገልፀዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳደሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ጥበብ ለአንድ ሃገር እድገት አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ ገልፀው የማህበረሰቡ ባህል፣ ታሪክና እሴት እንዲጠበቅና እንዲያድግ መሰል የውይይት መድረክ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በሃገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው የገጠር ኮሪደር ልማት ለጉራጌ ማህበረሰብ ትልቅ እድል እንደሆነ ያወሱት አቶ አበራ ለሌላው አብነት በሚሆን መልኩ በመስራት የቱሪዝም መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ የገቢ ምንጭ ለማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ።
የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ ጥበብ ለሰው ልጆች የተሰጠ ልዩ ችሮታና የአንድ ማህበረሰብ አኗኗር፣ ባህል፣ ታሪክ የተለያዩ ስሜቶችን በተለያየ መልኩ የሚገለፅበት ሃያል መሳሪያ መሆኑን ጠቅሰዉ በስእል፣ በድርሰት፣ በሙዚቃ፣ በግጥምና በውዝዋዜ መግለጽ ይቻላል ብለዋል።
ጥበብ ባህልን ለማሻገር ታሪክን ለማስተላለፍ ስሜትን ለመግለጽ ትልቅ መሳሪያ እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ መሰረት ኢትዮጵያ በጣሊያን ወረራ ወቅት ድል ስትቀዳጅ ኪነጥበብ የነበረው ድርሻ ከፍተኛ እንደነበረም ተናግረዋል።
ወ/ሮ መሰረት አክለውም የጉራጌ ማህበረሰብ ለሃገርና ለአለም የሚተርፉ ትልልቅ የጥበብ አሻራዎች እንዳሉት ገልፀው የመንደሩ አመሰራረትና የጀፎሮ አቀያየስ ስልት አንዱ ትልቅ የጥበብ ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል ።
የጉራጌ ብሔረሰብ የበርካታ ደራሲያን፣ ጋዜጠኞች፣ ፀሃፍቶች፣ አርቲስቶች መፍለቂያ በመሆኑ በዚህም ለሃገርና ለአለም የሚተርፍ ስራዎች እንደሰሩ ጠቁመው ከዚህም ባሸገር በእንጨት፣ በቆዳ፣ በቀንድ፣ በአለላ፣ በስንደዶ፣ በቃጫና በሌሎችም የተሰሩ የእደ ጥበብ ዉጤቶችን የማህበረሰቡ እሴት በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ ወ/ሮ መሰረት ተናግረዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሄኖክ ጉልላት እና ወጣት ዳኛቸው ፍቃዱ በሰጡን አስተያየት መድረኩ ጥበብን ለመጠበቅና የበለጠ ለማሳደግ እንዲሁም አቅምን ለማሳየት እድል የሚፈጥር እንደሆነ ገልፀዋል።
ዘጋቢ: ፍስሃ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል