ከ46 ሄክታር በላይ የወል መሬት በዘር መሸፈኑን በወላይታ ዞን የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” ለመሸጋገር ከተከናወኑ የበልግ ግብርና ሥራዎች ከ46 ሄክታር በላይ የወል መሬት በዘር መሸፈኑን በወላይታ ዞን የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በወረዳው በአስራ አንድ ቀበሌያት ከ46 ሄክታር በላይ የወል መሬት በዘር ተሸንፎ የሰብል እንክብካቤ እየተደረገ ይገኛል።

ከተረጂነት አስተሳሰብ በመውጣት የልማት መርሐ-ግብሮችን ተግባራዊ በማድረግ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለተቸገሩ ወገኖች በቂ ድጋፍ ለማድረግ፣ በዘላቂነትም ለማቋቋም ያልታረሱ የወል ምሬት በመጠቀም የግብርና ሥራን ማከናወን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው።

አርሶ አደር ተሾመ ሌራንሶ እና ፀጋዬ አታሮ በወረዳው የአድማንቾ አርፍጣ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከዚህ በፊት ያልታረሰ የወል መሬት በማረስ የበቆሎና ቦሎቄ ሰብል እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በህብረተሰብ ተሳትፎ የድህነት ቅነሳ ሥራ የሰብሎች ኩትኳቶ መቀጠሉን ያነሱት አርሶአደሮቹ ምርቱ መጋዘን እሰከሚገባ ድረስ የጥበቃ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እንዳልተለያቸውም ጠቁመዋል።

የወረዳው ግብርና ልማት ባለሙያ ሳሙኤል ላንቤቦ በበኩላቸው፤ ሁሉንም ህብረተሰብ ባሳተፈ መልኩ የተሠራው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የበልግ እርሻ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊ ግብአቶችና የሰብል እንክብካቤ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል።

በወረዳው ያሉት የሴፍቲኔት ተጠቃሚና በችግር ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ በህብረተሰብ ተሳትፎ 1.8 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ያነሱት በወረዳው ግብርና ጽ/ቤት የምግብ ዋስትና ሥራ ሂደት አስተባባሪ ምኖታ ለዓ፤ በበልግ እርሻ 46 ሄክታር በላይ ማሳ በበቆሎ ቦሎቄና በጎዳሬ መሸፈኑን አስረድተዋል።

በዘንድሮ በልግ እርሻ የወል መሬት ታርሶ 41 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የእርሻ ትራክተሮችን ከወላይታ ልማት ማህበርና አረካ ግብርና ምርምር ማዕከል ማግኘታቸውን የሚናገሩት የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ኦይቻ ኦሽኔ፤ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በአካባቢው ላይ ያሉት ፀጋዎችን በመጠቀም መለወጥ ይቻላል የሚሉት የወረዳው ብልግና ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መሰከረም አካለወልድ ናቸው።

ከተረጂነት ለመላቀቅ የሌማት ትሩፋት ሥራ በወረዳው አመርቂ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን