ትንቅንቅ

በፈረኦን ደበበ


ሰሞኑን ይሰማ የነበረው ከወትሮ ለየት ይላል፡፡ ውጥረት በበዛበት ዓለም የተለመደ ነው ከሚባለው ደረጃም በልጦ ተገኝቷል። በዓለም ህዝብ የሠላም ተስፋ ላይም ጥላ አጥልቶበታል፡፡
አዎን ጉዳዩ “የነብርን ጭራ ከያዙ ወደ ኋላ አይመለሱ” እንደሚባለው ነው፡፡ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ግለቱ ሲቀጥል ከግጭቱ ጋር ተያያዥ ነን ብለው እራሳቸውን የሚገልጹ አካላትም ወደ ፊት ለፊት እየወጡ ይገኛሉ። ለጦርነቱ ድጋፍ ላድርግ እንጂ በቀጥታ አልተሳተፍኩም የሚሉ ወገኖች ማንነትንም አጋልጧል፡፡
ቡድን 7 የተባለው የሀገራት ትብብር ደግሞ የሰሞንኛው ትርዒት አቅራቢ ሆነ። ከ2ተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ተመሥርቷል የተባለው ህብረት በኢንዱስትሪ የበለጸጉና የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አራማጅ የሚባሉ ሀገራትን አቅፏል፡፡ በዚህ መጠሪያ ዓለምን እያሽከረክሩ ሲቆዩ ከአመለካከታቸው ወጣ የሚሉትንም እየለየ ዱላውን ሲያሳርፉ መጥተዋል፡፡
ከህብረትነት አልፎ ምንም ዓይነት ህጋዊ ሰውነት የለውም የሚባልለት ቡድን ዓለም በውጥረት ውስጥ በነበረችበት የቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ የምዕራቡ ዓለም መለያ ሆኖ ያገለግል የነበረ ሲሆን ከሶቪየት ህብረት መፈረካከስ በኋላ ሩሲያንም ወደ አብራኩ አካትቶ ቡድን 8 የሚባል መጠሪያ አግኝቶ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሩሲያ እ.ኤ.አ. በ2014 የዩክሬንን ግዛት ወርራለች በሚል ቢፈነግላትም፡፡
አንዳንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ ሲል የቆየው ጥምረት በአሁኑ ጊዜ ግን በዓለም ላይ የተከሰተው ቀውስ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮልኛል በማለት በጠንካራ አንድነትና ዲስፕሊን እራሱን እየመራ ይገኛል፡፡ ቀውሶች የሚያስከትሏቸው ፖለቲካም ሆነ ማህበራዊ ለውጦችን በመግታት ያለውን ሥርዓት በማጠናከር ተግባር ላይ ተጠምዷል፡፡
በኃያላን ፍላጎት የሚመራና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቅምም በላይ መሆን የቻለው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከቅርብ ወራት ወዲህ አገርሽቶ የሁሉ ወገኖችን መስዋዕትነት እየጠየቀ ይገኛል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉትን ሁሉ አዳክሟል፡፡ በእንዲህ ከቆምኩበት ቦታ ተንሸራትቼ እንዴት እጅ እሰጣለሁ የሚል ቁጭትንም ፈጥሮባቸዋል፡፡
በዚህ ምክንያት ይመስላል የቡድኑ መሪዎች ጠንከር ያሉ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ የተነሳሱት፡፡ በየሀገሮቻቸው ላጋጠሙ ፖለቲካ ውድቀቶች መንስኤ ባሏቸው ጠላት ላይ ክንዳቸውን ለማሳረፍ የተገደዱት፡፡ በሩሲያ ላይ ቀድሞ ከተላለፉት ማዕቀቦች ጠንካራ የተባለውን ቀርጸውም ያስተላለፉት፡፡
በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በተጣለው የኒውክሌር ቦምብ ክፉኛ በተደቆሰቺው የጃፓኗ ሂሮሽማ ከተማ ሰሞኑን የተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ በብዙ መልኩ ተመሳሳይ እልቂትን የሚያስቀር ተብሎ ቢነገርም የተላለፉ ውሳኔዎች ሥጋትን ሁሉ የዘሩ ሆነዋል፡፡ ጠላቶች ተብለው በተፈረጁ ሀገራት ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ የማዕቀብ ናዳም አውርደዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት፣ የተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካዮችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችን የያዘው ያሁኑ የቡድኑ ጉባኤ የአሜሪካ፣ የፈረንሳይ፣ የካናዳ፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ ጀርመንና የእንግሊዝ መሪዎችን ያካተተ ሲሆን ዓላማውም በሩሲያና ዩክሬን ጦርነትና እንዲሁም በልማትና ሌሎች ሰብአዊ ድጋፎች ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ባሉ ሁለት ቀናት በተደረገው ጉባኤ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የታደሙ ሲሆን በዚህ ከጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትርና ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጋርም ፊት ለፊት ተወያይተዋል። የመጀመሪያው ቀን ዋና አጀንዳ በሩሲያ ላይ በሚጣለው ማዕቀብ ላይ ትኩረት ሲያደርግ የሁለተኛው ቀን ደግሞ በልማትና በዓለም ዙሪያ በሚከናውኑ የድጋፍና እርዳታ ተግባራት ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡
አልጀዚራና ቢቢሲ የጉባኤውን ሂደት ተከታትለው እንዳቀረቡት ዘገባ ከሆነ በጉባኤው መክፈቻ ላይ መሪዎቹ ቻይና ልትጫወት በምትችላቸው ሚና ላይም ጥሪ አድረገውላታል በተለይ ለሩሲያ ካላት ቀረቤታ አንጻር በመምከር እንድትመልሳት በመማጸን።
ሌላው በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ሲሆን ከገቢና ወጪ ዕቃዎች ጀምሮ ገንዘብ አግኝታ ጦርነቱን ትገፋበታለች ያሏቸው የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች፣ ማዕድናት፣ የብረታ ብረት መለዋወጫዎች፣ ንግድ፣ አስቀድሞ የተላለፉ ማዕቀቦችን ተላልፈው ለሀገሪቱ ድጋፍ እያደረጉ ባሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁም በግለሰቦችና ቡድን ሀብቶች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በዚህ ዙሪያ አስተያታቸውን ለቢቢሲ የሰጡት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ረሺ ሱናክ ሁሉም ሀገራት “እኛን ተከትለው ማዕቀቡን ያጠናክሩ” የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡
እስካሁን ድረስ በተለያዩ ደረጃዎች የተጣሉ ማዕቀቦች የረባ ተጽዕኖ እንዳልፈጠሩ በስፋት እየተነገረ ባለበት ወቅት የሚጣለው ማዕቀብ ውጤታማ መሆኑ አጠራጣሪ ቢሆንም በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ስም ባሉ ሀብቶች ላይም በርካታ ዕገዳዎች ተጥለዋል እያንዳንዱ ገቢና ወጪን ባነጣጠረ አኳኋን፡፡
ከቡድኑ አለፍ ተብሎ ሲታይ አሜሪካ በራሷ የጣለቻቸው ማዕቀቦችም እንደዚሁ በርካታ ሲሆኑ የተለያዩ የገቢ፣ ወጪ፣ የማምረቻና ንግድ እንዲሁም ግለሰቦች ላይ ትኩረት ያደረጉም ናቸው በተለይ ውሳኔው የማዕቀቡ ጠንሳሽና አቀንቃኝ ለሆኑት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እፎይታ የሚሰጣቸው ከሆነ፡፡
ከማዕቀቡ ጉዳይ ወጣ ሲባል መሪዎቹ አጽንኦት የሰጡት ከቻይና ጋር ሊደረግ ስለሚገባው ውይይትና ትኩረት ሲሆን በዚህ መንገድም ከሀገሪቱ ጋር የገቡበትን ውዝግብ ገልጸዋል፡፡ እየዳበረ ያለውን የምጣኔ ሀብት አቅሟን በመጠቀም በሌሎች ላይ ጫና እንዳትፈጥር በማለት፡፡
ችግሩ አሁን አሁን በስፋት እየተነገረ ካለው የቻይና “ዛቻ” ጋርም የሚገናኝ ሲሆን በአካባቢው ሀገራትና በሌሎች አካባቢዎችም ሥጋት ከምትሆንባቸው ድርጊቶች እንድትታቀብ አስጠንቅቀዋታል በቅርቡ የእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ታይዋንን ከጎበኙ በኋላ ጠንከር ያለ አቋም እንዲወሰድባት የጠየቁበት ሳይረሳ፡፡
ከማዕቀቡ ጋር የተያያዙና ሌሎች ጉዳዮችንም ከተመለከትን ሰሞኑን የቡድን 7 አባል ሀገራት እያሳለፉት ያለው ውሳኔ የመጨረሻ የሞት ሽረት እርምጃ ተደርጎም ይወሰዳል ምክንያቱ ያለ የለሌ ኃይላቸውን ተጠቅመው ሩሲያን በበቂ ሁኔታ መግታት፤ ካልተቻለም ጠራርጎ ከዩክሬን ምድር ማስወጣት የሚል አቋም ስላላቸው፡፡
ለዚህ ደግሞ ዩክሬን እያሰበችበት ያለውና ከባድ የተባለለት የጸረ-ማጥቃት እርምጃ ተጠቃሽ ሲሆን ባለፉ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ብቻ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ባደረጓቸው ጉብኝቶች በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል በመግባትና ሰጥተው ተግባራዊ ያደረጉም አሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ጦርነቱ ምን ያህል እስከ መጨረሻው ግለት እንደደረሰም ያሳያሉ።
አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዩክሬን ለመስጠት ቃል የገባችውና ሩሲያም ጠንከር ባሉ ቃላት ያወገዘችው የኤፍ,16 ተዋጊ አውሮፕላን ድጋፍ በዚህ ውስጥ ይካተታል፡፡
በዚያም ሆነ በዚህ ሲታይ የአሁኑ የቡድን 7 መሪዎች መፍጨርጨር ተፎካካሪ የተባሉ ሀገራትን ለመቅጣት የተነሳሳው ያህል የራሳቸው የሞት ዕድልንም ሊያሰፋ እንደሚችል አዲስ ከሚወጡ መረጃዎች እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ ከሀገር ቤት ፖለቲካ እስከ ዩክሬን፣ ሩሲያን አልፈው እስከ ቻይና የዘረጉት ረጅም እጅም ከሁኔታዎች መወሳሰብ የተነሳ ወደፊት የሚስፈነጥር ሳይሆን ወደ ኋላ የመኮማተር አደጋ ሁሉ ስለሚኖረው፡፡
ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ከኒውክሌር የጸዳ ዓለም እንገነባለን እያሉና በሂሮሽማ የኒውክሌር ተጠቂዎች መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ባኖሩበት ቅጽበት ሌላ የጸብ ጫሪ ድርጊት መፈጸማቸው ነው፡፡ ቻይና ሩሲያን እንድታግባባ በአንድ በኩል ተማጽኖ እያቀረቡ በሌላ በኩል ባለ በለሌ ኃይል ቻይና ላይ እርምጃ ለመውሰድ መነሳሳታቸው ነው። ሩሲያ ሰሞኑን ከረጅም ወራት ጀምሮ ስትፋለም የቆየችበትን የዩክሬን ባክሙት ከተማ መቆጣጠሯም መያዣ መጨበጫ ያሳጣቸው ይመስላል፡፡