በወረዳው በተያዘው የበልግ እርሻ ከ26 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑ ተገለጸ

በወረዳው በተያዘው የበልግ እርሻ ከ26 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፋርዳ ወረዳ በተያዘው የበልግ እርሻ ከ26 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የወረዳው ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በወረዳው በበልግ ልማቱ ከ16 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ሰብል መሸፈኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

አቶ ደስታ ሻሎ፣ አቶ ፋጂ መሴና አቶ መለሰ አበራ በጉራፈርዳ ወረዳ የሴጋና ኦቱዋ ቀበሌ አርሶ አደሮች ናቸው።

አርሶ አደሮቹ በዘንድሮው የበልግ ወራት ያላቸውን መሬት በቴክኖሎጂ ታግዘው በበቆሎ ሰብል መሸፈናቸውን ተናግረዋል።

እያለሙ ያለው የበቆሎ ሰብል በአሁኑ ወቅት ጥሩ በሚባል መልኩ የሚገኝ ቢሆንም በአካባቢው ፀሀይ በመብዛቱ ተባይ መከሰቱን ጠቁመው የተከሰተው ተባይ በሰብሉ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በባህላዊ መንገድ የመከላከል ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በዘንድሮው አመት በበልጉ የምርጥ ዘርና የግብአት አቅርቦት ችግሮች አጋጥሞአቸው እንደነበረ የተናገሩት አርሶ አደሮቹ በሚቀጥለው የመኸር ወቅት ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

የጉራፈርዳ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አሸናፊ ዘሪሁን እንደተናገሩት በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከ26 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ዋና ዋና ሰብሎች ተሸፍነዋል።

በወረዳው በቆሎ፣ ሩዝ፣ ሰሊጥና ቦሎቄ እንዲሁም ኑግና ሱፍን ጨምሮ በርካታ የሰብል አይነቶች በበልግ እርሻው በመልማት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በወረዳው ሰፊ ሽፋን የያዘው የበቆሎ ሰብል ሲሆን ይህም ከ16 ሺ ሄክታር በላይ መሬት መሆኑን አንስተዋል።

በወረዳው በተፈጠረው የዝናብ መዘግየት የተነሳ ተባይ መከሰቱን የተናገሩት አቶ አሸናፊ በተደረገው ልየታ 632 ሄክታር መሬት ላይ ተባይ መታየቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተከሰተው ተባይ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር 466 ሄክታር በባህላዊና 165 ሄክታሩን ማሳ ደግሞ በዘመናዊ የኬሚካል ርጭት በማከናወን ለመከላከል የሚያስችል ስራ እየተሰራ እንዳለም አብራርተዋል።

የጉራፈርዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስንታየሁ ከርካ በበኩላቸው በወረዳው የበልግ ስራ ውጤታማ እንዲሆንና አሁን ላይ ያለውን የሰላምና ልማት ስራ በዘላቂነት ለማስቀጠል እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን