የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለውጥ የሚበጅ፤ ዘመኑን በሚዋጅ የቴክኖሎጂ እውቀት የበለጸጉ ዜጎች የሚፈልቁበት ተቋም ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለውጥ የሚበጅ፤ ዘመኑን በሚዋጅ የቴክኖሎጂ እውቀት የበለጸጉ ዜጎች የሚፈልቁበት ተቋም ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ

ይህንን የገለጹት ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን ተማሪዎች ባስመረቀበት ወቅት ነው።

ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በእንሰሳት ጤና የትምህርት ዘርፍ በዶክተሬት ዲግሪ ተማሪዎችን አስመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ ሀገሪቱ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እየተሻገረች በምትገኝበት ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ትልቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲም ለ4ኛ የኢንደስትሪ አብዮት መሳካት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በ3 ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እየሰራ ሲሆን በየግብርና ልማት፣ በቱሪዝምና ሀገር በቀል ዕውቀት ማልማትና የድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዋንኞቹ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ተመራቂዎችም ዲግሪ የዕውቀት ምልክት ብቻ ሳይሆን የሀገር ልማት ኃላፊነት ጭምር እንደሆነ መገንዘብ አለባችሁ ያሉት ዋና አፈ ጉባኤው፤ ብቁና ተወዳዳሪነታችሁን ለሀገራችሁ ብልጽግና ማዋል ይኖርባችኋልም ሲሉ መክረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ በበኩላቸው፤ ዛሬ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ታላቅ ቀን፤ ለተመራቂዎችም የአዲስ ኃላፊነትና የተስፋ ቀን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ለማሻሻል እየተሰራ ባለበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው በ29 የትምህርት መርሃ ግብሮች ክለሳና ማሻሻያ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም በዚሁ ወቅት ጠቅሰዋል።

በምርምር ዘርፍም 50 ያክል ስራዎች መጀመራቸውን በማንሳት በተለይም በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መስክም ዩኒቨርሲቲው ለአለማቀፋዊነት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የተሻለ ውጤት ላመጡ ተማሪዎችም ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን