በመስኖ ልማት ውጤታማ ሆነናል -በሀዲያ ዞን የምዕራብ ሶሮ ወረዳ አርሶ አደሮች

የተለያዩ የውሃ አማረጮችን በመጠቀም በበጋ መስኖ የጓሮ አትክልቶችንና የበቆሎ ሰብል በመምረት ከራሳቸው አልፈው ለገበያ ጭምር በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደማገኙ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ምዕራብ ሶሮ ወረዳ የሚገኙ አንዳንድ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ተናገሩ፡፡

የወረዳው ግብርና ልማት ጽ/ቤት በበኩሉ ከ2ሺ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት ከ3መቶ 62ሺ ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት መታቀዱን አስታውቋል፡፡

በወረዳው በቀበርቡያ እና ኦርጫ ቀበሌያት ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮችና ወጣቶች እንደገለጹት በበጋ መስኖ ስራ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የጓሮ አትክልቶችንና የበቆሎ ሰብል በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

አርሶ አደሮቹና ወጣቶቹ ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ላይ በሀገሪቱ ብሎም በአከባቢው እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም በትጋት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል::

በቀበር-ቡያ ቀበሌ ያነጋገርናቸው ወጣቶች እየተጠቀሙት ያለው መስኖ ውሃ በባህላዊ መንገድ በመሆኑ የመንግሥት አካላት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ወደ ዘመናዊ መስኖ በመቀየር የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የምዕራብ ሶሮ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ታምራት በበኩላቸው በወረዳው በዘንድሮ የምርት ዘመን በበጋ መስኖ 2ሺ 10 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የውሃ አማረጮችን በመጠቀም የጓሮ አትክልቶችንና የተለያዩ ሰብሎችን እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምርት ዘመኑም ከ3 መቶ 62 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ተቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ኃላፊው ጠቁመዋል ።

አርሶ-አደሮቹ ያመረቱትን በተገቢ ዋጋ እንዲሸጡ ከንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ጋር ትስስር በመፈጠሩ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

አርሶ-አደሮቹና ወጣቶቹ ያነሱትን ችግሮች ለመቅረፍ ከዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰዋል::

የምዕራብ ሶሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ዶዕሌቦ በወረዳው ያሉ እምቅ የግብርና ፀጋዎችን በመለየት የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በማምረት ማህበረሰብን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሻገር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን በመቅረፍ ማህበረሰቡን በምግብ ራስን ወደ መቻል ደረጃ ለማሻገር ከአመለካከት ጀምሮ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ መስራት እንዲችሉ በማድረግ አበረታች ለውጥ መምጣቱን አንስተው አሁን ላይ ዘመናዊ የግብርና መካናይዜሽን በተከተለ መልኩ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተጀመረውን የግብርና ስራ በማጠናከር በመጪው የበልግ ወቅት ከ 4 ሺህ 6 መቶ ሄክታር በላይ ማሳ በሆርቲካልቸር እና በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለመሸፈን ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸው ተመላክቷል።

ዘጋቢ : በየነ ሰላሙ-ከሆሳዕና ጣቢያችን