ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ሲሉ የቡርጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኮሬ አዶ ገለፁ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ፣ ፕላንና ልማት ቢሮ፣ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ እና በፋይናንስ ቢሮ የተመራ ልዑክ በቡርጂ ዞን ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመደበኛና ካፒታል ፕሮጀክቶች የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

በመስክ ምልከታ ወቅት የቡራቡርጄ ገበያ ማዕከል፣ ወልዴና ተንጠልጣይ ድልድይ፣ በሶያማ ከተማ የተጀመረው የዲች ግንባታ እና በርካታ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው በመመልከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካራ ማሞ፤ የተቋረጡ እና ያላለቁ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው በማስገንዘብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

የመሰረተ ልማት እጥረት ባለበት የፕሮጀክቶች መቋረጥ አግባብ አይደለም ያሉት የቡርጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳኜ ህዶ፤ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በትብብር በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

መንገድ፣ ንፁህ መጠጥ ውሃ እና መስኖ ወሳኝ ከሚባሉ መሠረተ ልማቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸዉን ያነሱት የቡርጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኮሬ አዶ፤ እነዚህንና ሌሎች ግንባታቸዉ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች በበኩላቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ: አሀዱ አሸናፊ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን