ከበልግ እርሻ ሰብሎች 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ማቀዱን የቡርጂ ዞን ገለጸ

ከበልግ እርሻ ሰብሎች 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ማቀዱን የቡርጂ ዞን ገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከበልግ እርሻ በሆርቲካልቸር እና አዝርእት ሰብሎች አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ማቀዱን የቡርጂ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

ከታረሰው መሬት 74 ሺህ 144 ሄክታር (87%) በዘር መሸፈኑን የተናገሩት የቡርጂ ዞን የግብርና መምሪያ ተወካይ እና የአዝርዕት ሰብሎች ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ቦጋለ ጅራ ከበልግ እርሻ በሆርቲካልቸር እና አዝርእት ሰብሎች አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ማቀዱን አስታውቀዋል።

የአፈር ማዳበሪያ ዕጥረት በክልል ደረጃ መኖሩን ያነሱት አቶ ቦጋለ የአቅርቦት ችግርን ለመፍታት በየጊዜው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልፀው ከዚህ ጎን ለጎን አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲጠቀም ግንዛቤ መፈጠሩን አብራርተዋል።

በቂ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መቅረቡን የተናገሩት ተወካዩ በየጊዜው ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን አክለው ገልፀዋል።

በቡርጂ ዞን ሶያማ ዙሪያ ወረዳ ጎቼ ክላስተር የመስክ ምልከታ ሲያደርጉ አግኝተን ያነጋገርናቸው የቡርጂ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዑመር ጭላሌ የበልግ አዝመራ በጥሩ ሁኔታ ላሉ እንደሚኝ ገልጸው አርሶአደሩ ግብአት በስፋት ስለሚፈልግ አቅርቦት ላይ በትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል።

አቶ ታምራት ባሳዬ እና አሮሳ ናኖ በቡርጂ ዞን ሶያማ ዙሪያ ወረዳ የራለያ ኩሮ እና ዶልቻ ቀበሌ አርሶ አደሮች ሲሆኑ፥ የበልግ አዝመራ በጥሩ ደረጃ እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ዝናብ በወቅቱ ካገኘን እና በቂ ማዳበሪያ ከተገኘ ምርታማ እንሆናለን ሲሉ የገለጹት አርሶአደሮቹ በወቅቱ የተዘራው ሰብል ማዳበሪያ እንደሚፈልግ እና በሚፈለገው ልክ እያገኙ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አሀዱ አሸናፊ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን