ወጣቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ የነገ ህይወቱ ተቀይሮ ለሀገር እንዲተርፍ ክህሎቱን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተገለጸ

ወጣቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ የነገ ህይወቱ ተቀይሮ ለሀገር እንዲተርፍ ክህሎቱን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተገለጸ

የጌዴኦ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የ9 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በይርጋጨፌ ከተማ አካሂዷል።

ከወጣቱ ሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የታቀዱ ጉዳዮች በአግባቡ ስለመሰራታቸው ጠንካራና ደካማ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት ውይይት ማካሄዳቸውን የጌዴኦ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ ተናግረዋል።

በዞኑ 54 ሺህ ሥራ አጦች የመለየት ሥራ መሠራቱን የገለጹት አቶ ተገኝ፤ 40 ሺህ የሚሆኑት በቋሚና ጊዜያዊ ሥራዎች መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።

ወጣቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ የነገ ህይወቱ ተቀይሮ ለሀገር እንዲተርፍ ክህሎቱን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ እንዳለም ገልጸዋል።

የሥራ አጥ ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ በሀገር ውስጥ ብቻ ችግሩን መቅረፍ አይቻልም የሚሉት አቶ ተገኝ መንግስት፤ ስምምነት በተፈራረመባቸው የውጪ ሀገራት በህጋዊ የሥራ ስምሪት እንዲሳተፉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በማንሳት ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት የውይይቱ ተሳታፊዎች ቀጣዩ ጊዜ በውጤት የታጀበ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ሴቶች በሥራ ዕድል ፈጠራ በግብርናውና በንግዱ ተሳታፊ በመሆን ከጥገኝነት መውጣት አለባቸው ያሉት የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያ ኃላፊና የውይይቱ ተሳታፊ ወ/ሮ ፍሬነሽ አየለ፤ ለሌላው አርአያ መሆን የሚችሉ በርካታ ሴቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ሥራ ዕድል ፈጠራ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ያሉት ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊና የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን፤ በከተማው በርካታ ሀብት በመኖሩ ወጣቱ ሥራ ሳይንቅ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ: ውብሸት ከሣሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን