የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የትምህርት ግበዓት መሟላት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የትምህርት ግበዓት መሟላት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የትምህርት ግበዓት መሟላት ወሳኝ መሆኑን በአሪ ዞን የጂንካ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

‎“የሚያነብ ትውልድ ነገውን ያንፃል” በሚል መሪ ሀሳብ በጂንካ መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማርያና አጋዥ የመፀሐፍ ማሰባሰብ ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

‎የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሽ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የትምህርት ግበዓት መሟላት ወሳኝ በመሆኑ በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ የሚኖሩ በጎ ፍቃደኞች እየተከናወነ ያለው መፀሀፍ የማሰባሰብ ዘመቻ፥ የመንግስትን ስራ አጋዥ በመሆኑ በቀጣይ የተማሪዎችን የማንበብ ክህሎት ለማሳደግና በተደራጀ መልኩ የመማር ማስተማሩን ስራ ለማጠናከር ዘመናዊ ላይብሬሪ ለመገንባት አስፈላጊዉ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

‎የጂንካ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ውባለም ገዛኸኝ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሁሉም ርብርብ ስለሚያስፈልግ በጎ ፍቃደኞች ለሚያደረጉት የመፀሐፍ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

‎በጂንካ ዩኒቨርስቲ የጥናትና የምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪ ዶ/ር ኬሮ አሰፋ በበኩላቸዉ በእውቀት የሚመራ በምክንያት የተደራጀና የሚያነብ ትዉልድ ለመፍጠር መፀሐፍ አስፈላጊ በመሆኑ በጎ ፍቃደኞች ያደረጉት የመፀሐፍ ድጋፍ የሚበረታታ በመሆኑ ዩኒቨርስቲዉም አስፈላጊዉን ድጋፍና እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡

‎በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የተጀመረዉ የመፀሐፍ ማሰባሰብ ስራ ለትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማ ሂደት የሚያግዝና የመምህራንን አቅም የሚገነባ መሆኑን የገለፁት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ወ/ሮ ሽቱ ሻሆ ናቸዉ ፡፡

‎የሚያነብ ትዉልድ ነገዉን ያንፃል በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረዉ የመፀሐፍ ማሰባሰብ ዘመቻ የተሻለ ትውልድ ለመቅረፅ ያለመ በመሆኑ ከመፀሐፍ ማሰባሰቡ ዘመቻ ጎን ለጎን በትምህርት ቤቱ ግቢ ዉስጥ የላይብረሪ ግንባታ መጀመሩን ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡

ዘገቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን