በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 57 ሺህ 241 ተማሪዎች የ2017 ብሔራዊ ፈተናን ለመፈተን መመዝገባቸው ተገለፀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 57 ሺህ 241 ተማሪዎች የ2017 ብሔራዊ ፈተናን ለመፈተን መመዝገባቸው ተገለፀ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 57 ሺህ 241 ተማሪዎች የ2017 ብሔራዊ ፈተናን ለመፈተን መመዝገባቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ከነዚህ መካከልም 7ሺህ 942 ተማሪዎች በበይነ መረብ ፈተናውን እንደሚፈተኑ ተጠቁሟል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊና የመማር ማስተማር ምዘና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ በክልሉ 57 ሺህ 241 ተማሪዎች የ2017 ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለመፈተን መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

‎በ2016፥ 1ሺህ 958 ተፈታኞች በበይነ መረብ ፈተናውን መውሰዳቸውን ጠቁመው፥ ዘንድሮ 7ሺህ 942 ተማሪዎች ፈተናውን በበይነ መረብ ይወስዳሉ ብለዋል።

‎በተያዘው የትምህርት ዘመንም ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና ተስፈኛ ተፈታኞችን በማህበራዊና በተፈጥሮ ሳይንስ ለማስፈተን ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል።

‎እነዚህ ተማሪዎች በክልሉ በሚገኙ 57 ትምህርቶ ቤቶች እና በ4ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናውን እንደሚወስዱና ለዚህም ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጭምር አቶ ኢሳያስ ጠቁመዋል።

‎የቀድሞ የምዘና ስርዓት የጋሸበና ኋላ ቀር እንደነበረ ያስታወሱት ኃላፊው፥ ዘንድሮ ያሉ ጉድለቶችን ለማረም በየደረጃ ከሚገኙ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጭምር አረጋግጠዋል።

‎ዘጋቢ፡ ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባምንጭ ጣቢያችን