ባለፉት አራት አመታት በክልሉ 270 የውሃ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ

ባለፉት አራት አመታት በክልሉ 270 የውሃ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የ2017 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻፀም ግምገማና የቀጣይ 3 ወራት ትኩረት አቅጣጫ ላይ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳና በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ እና የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ፤ ባለፉት አራት አመታት በክልሉ 270 የውሃ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በክልሉ ያለውን የግብርና ዘርፍ አቅሞች ወደ ምርትና ምርታማነት ለመቀየር አርሶ አደሩን ከተለመዱ የእርሻ ሥራዎች በማላቀቅ የውሃ አማራጮችን እንዲጠቀም ማስቻል አሰፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከዚህ ቀደም ከነበረበት መሻሻል ቢያሳይም ከተደራሽነት አኳያ ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል ያሉት አቶ ነጋ አበራ፤ በቀጣይ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎን ማጠናከርና የተጀመሩ ተግባራት ማከናወን ወሳኝ ነው ብለዋል።

ክልሉ በከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ ሀብት የታደለ ቢሆንም በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር ያለውን ማነቆ መፍታት እንደሚጠበቅ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው ናቸው፡፡

ክልሉ ሲመሰረት የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 32 ነጥብ 7 በመቶ ሲሆን ባለፉት አራት አመታት በተደረገው ርብርብ ወደ 44 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

45 ትላልቅ ፕሮጀክቶች በክልሉ መንግስት፣ 108 አነስተኛ ኘሮጀክቶች በዞንና ወረዳ በጀት ማጠናቀቅ መቻሉን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊው፤ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች 112 እና በማህበረሰቡ ተሳትፎ 5 ኘሮጀክቶች በጠቅላላው ከ270 በላይ የተለያየ ደረጃ ያላቸው የውሃ ፕሮጀክቶች ተገብንተው አገልግሎት መስጠታቸውን አስረድተዋል።

የውሃ ግንባታዎች በመጠናቀቃቸው ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ኢንጂነር በየነ በላቸው የገለጹት።

በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ 26 የውሃ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ከ150 ሺህ በላይ የክልሉ ህብረተሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲያደርግ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው ሃላፊው የተናገሩት።

ቢሮው ከሚያከናውናቸው አበይት ተግባራት መካከል አርሶ አደሩ የዘመናዊ መስኖ አውታሮችን በመጠቀም ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት የውሃ አማራጮች ተጠቃሚ እንዲሆን በተደረገው ጥረት ባለፉት 4 አመታት 15 አነስተኛ የመስኖ ኘሮጀክቶች አገልግሎት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የመስኖ ተቋማትን ወደ 77 ከፍ ማድረግ ተችሏል ያሉት ኢንጂነሩ፤ በተጨማሪም 11 በግንባታ ሂደትና 15 የጥናትና ዲዛይን ሂደት ላይ ያሉትን በማጠናቀቅ ክልሉን የዘመናዊ መስኖ አውታሮች ባለቤት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርሶ-አደሩም ዘመኑ የሚመጥነውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድግ በትጋት ይሰራል ብለዋል።

በመሆኑም በአፈጻጸም ወቅት የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት ውጤት በሚያስገኙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል በማለት ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን