ግሎባል ፋይናንስ ባካሄደው የ2025 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የባንኮች ውድድር አዋሽ ባንክ ከ36 የአፍሪካ ምርጥ ባንኮች አንዱ በመሆን እውቅና ማገኘቱ ተገለፀ

ግሎባል ፋይናንስ ባካሄደው የ2025 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የባንኮች ውድድር አዋሽ ባንክ ከ36 የአፍሪካ ምርጥ ባንኮች አንዱ በመሆን እውቅና ማገኘቱ ተገለፀ

የባንኩ ሲኒየር ቺፍ ማርኬቲንግ ኦፊሰር አቶ ዮሐንስ መርጋ እውቅናውን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አዋሽ ባንክ እ.አ.አ በ2025 ግሎባል ፋይናንስ ባካሄደው ዓለም አቀፍ የባንኮች ውድድር አዋሽ ባንክ ከአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ባንክ ተብለው ከተመረጡ 36 ባንኮች መካከል አንዱ በመሆን ከኢትዮጵያ ብቸኛው ባንክ ሆኖ ለ4ኛ ጊዜ መመረጡን አስታውቀዋል።

አዋሽ ባንክ የዓመቱ ምርጥ ባንኮችን በመቀላቀል ዕውቅና ለማግኘት የቻለው የዓመታዊ ትርፍ፣ በብድር አቅርቦት መጠን፣ በትርፍ ክፍፍል ተደራሽነት፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እና ባንኩ ለደንበኞቹ በሚሰጠው አገልግሎት፣ በደንበኞች ብዛትና በገበያ ድርሻ ዕድገት፣ ዘመኑን በሚዋጁ አዳዲስ አገልግሎቶች የመሳሰሉትን የግሎባል ፋይናንስ የማወዳደሪያ መስፈርቶችን በማሟላቱ እንደሆነ አቶ ዮሐንስ ገልፀዋል።

አቶ ዮሐንስ አክለውም የተለያዩ የፋይናንስ ዘርፍ ተንታኞችና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች ለአዋሽ ባንክ የሰጡት ድምፅ ለባንኩ ዕውቅና ማግኘት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደነበረው ተናግረዋል።

አዋሽ ባንክ ያገኘው እውቅና በኢትዮጵያ የባንኮች ዘርፍ መነቃቃትን የሚፈጥርና ሌሎች ባንኮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ዘጋቢ፤- ንጋቱ ወልዴ