የግብርናን ምርትና ምርታማነት ማዘመንና ማሳደግ ዘላቂ ልማትን እና የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑ ተጠቆመ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዮስ አኒዮ ከዞኑና ከምስራቅ ባደዋቾ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በዞኑ ምስራቅ ባደዋቾ ወረዳ የበልግ ግብርና በማስጀመር በክላስተር ኩታ ገጠም እየተዘሩና እየለሙ ያሉ የበቆሎ ማሳ መስክ ምልከታ አድርገዋል።
በበልግ ግብርና ማስጀመሪያ እና መስክ ምልከታ ወቅት ዋና አስተዳዳሪው እንደገለጹት፤ የግብርናን ምርትና ምርታማነት ማዘመንና ማሳደግ ዘላቂ ልማትን እና የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አማራጭ የሌለው ተግባር ነው።
የመስክ ምልከታ ዓላማው በሪፖርት የሚቀርባው የግብርና ስራን ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሆነም አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል።
ለዚህ ስኬት በዘንድሮው ለበልግ ግብርና የሚውል በቂ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በወቅቱ መቅረቡን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪ በአሁኑ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ዕጥረት የገጠመው አንድም አርሶአደር አለመኖሩን አመላክተዋል።
በዕለቱ በዞኑ በምስራቅ ባደዋቾ ወረደ በ6 ከላስተሮች በ335 ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም የበልግ በቆሎ እየተዘራ መሆኑና ከዚህ ቀደም ተዘርቶ የበቀሉ የበቆሎ ሰብል ውጤታማ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ ይህም በአርሶ አደሮች ዘንድ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተት አለመኖሩን አመላካች ነው ብለዋል።
አርሶ አደሩ የቀረበውን የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ጥምርታን ጠብቆ በመዝራት እና አረምንና ተባይን በተገቢው በመቆጣጠር ምርትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት መስራት አንዳለባት አቶ ማቲዎስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሀብታሙ ታደሰ በበኩላቸው፤ በዓመቱ ከ90 ሺህ 812 ሄክታር በላይ ማሳን በበልግ በማልማት ከ8 ሚሊየን በላይ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ31ሺህ በላይ ሄክታር ማሳ በክላስተር በማልማት ከ3ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ዶክተር ሀብታሙ ጠቁመዋል።
ለበልግ ግብርና የሚውል 1መቶ 11ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ የገባ ሲሆን ከዚህም እስካሁን ከ90ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶአደሮች ተሰራጭቷል ብለዋል።
አርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ እንዲዘራ በባለሙያዎች የምክር አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ዶክተር ሀብታሙ ተናግረዋል።
በወረዳው በተለያዩ ቀበሌያት በክላስተር ተደራጅተው በኩታ ገጠም የበልግ በቆሎ በመዝራት ላይ የነበሩ አርሶአደሮች በሰጡት አስተያየት፤ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በወቅቱ እና በፍላጎታቸው መሰረት አግኝተው በወቅቱ የበልግ ግብርና እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ መጋቢት 26/2017 ዓ.ም #ደሬቴድ – ቀጥታ ስርጭት
ባለፉት አራት አመታት በክልሉ 270 የውሃ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ
ግሎባል ፋይናንስ ባካሄደው የ2025 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የባንኮች ውድድር አዋሽ ባንክ ከ36 የአፍሪካ ምርጥ ባንኮች አንዱ በመሆን እውቅና ማገኘቱ ተገለፀ