ኅብረተሰቡ በመሠረተ ልማት ዙሪያ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በተግባር ለመመለስ በትኩረት እየሠራ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔን ጨምሮ የሥራ ኃላፊዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት የቱሊሴ-አርቻ የድልድይ ግንባታ ሥራ በይፋ ተጀምሯል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን በዲላ ዲስትሪክት አማካኝነት የሚገነባው የሃዳ ወንዝ የድልድይ ግንባታ ሥራ ፕሮጀክት በ1 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአካባቢው ሕብረተሰብ በይፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የዲስትሪክቱ አስተባባሪ አቶ ፍሰሃየሱስ ካሳዬ ተናግረዋል።
የድልድዩ ግንባታ ሥራ ቢበዛ ከ2 ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለአካባቢው ሕብረተሰብ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የገለጹት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን የዲላ ዲስትሪክት አስተባባሪ፤ ለግንባታው ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን ተናግረዋል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ፤ ኅብረተሰቡ በመሠረተ ልማት ዙሪያ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን በተግባር ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልፀው በወረዳው ከድልድዮች ግንባታ ባለፈ 16 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በወረዳው እየተሠሩ ባሉ መሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ የወረዳው አስተዳደር ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማድረግ ባለቤትነቱን እንዲያረጋግጥ የማድረግ ሥራ መሆኑን ጠቁመው የፋብሪካ ውጤት ያልሆኑ የእንጨት ውጤቶችን በማዋጣት በግንባታው በመሳተፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ አስተዳዳሪው ጠይቀዋል።
የወረዳው ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ዋቆ፤ በወረዳው ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ የአዳዲስ መንገድ ከፈታና ጥገና ለማድረግ መታቀዱን ገልፀው አፋጣኝ ጥገናና ግንባታ የሚያስፈልጋቸውን መንገዶችና ድልድዮችን በመለየት በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በሃዳ ወንዝ ላይ ድልድይ ባለመገንባቱና የክረምት ዝናብን ተከትሎ በሚከሰተው ወንዝ ሙላት ምክንያት ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ከመዳረጉ ባለፈ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማድረስና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ለማግኘት ሲቸገሩ እንደነበር ገልፀዋል።
የወረዳው አስተዳደር የገባውን ቃል በተግባር እየመለሰ መሆኑን የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ ግንባታው መጀመሩ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ክልሉ ከተደራጀ ጀምሮ በሁሉም መዋቅሮች በግብዓት አቅርቦት እና ተደራሽነት የተሻለ ተግባር መኖሩ ተገለጸ
8ኛው ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለዘላቂ ሠላም በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የምርምር ዐውደ ጥናት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ይገኛል
የፌደራል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የባስኬቶ ዞን ተወላጆች አንድነት እና ወንድማማችነት ማጠናከሪያ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል