በበጎ ፈቃድ ለ35ኛ ጊዜ በደም ልገሳ ፕሮግራም ላይ መሳተፋቸውንና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ ዳይሬክቶሬት ሲዲሲ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ታከለ ወ/ጊዮርጊስ ገለጹ፡፡
ዶ/ር ታከለ ወ/ጊዮርጊስ ይህንን ያሉት በክልሉ ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ በሚገኘው የቦንጋ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ተገኝተው ደም በለገሱበት ወቅት ነው፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደም የሚለግሱ ሰዎች ከማይለግሱት ጋር ሲነፃፀሩ በድንገተኛ የልብ ሕመምና ለካንሰር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው፡፡
ዶ/ር ታከለ ወ/ጊርጊስ አያይዘውም፤ በደም ልገሳ ተግባር ለ35ኛ ጊዜ መሳተፋቸውንና በሰጡት አንድ ዩኒት ደም የ3 ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በ2004 ዓ.ም በይርጋለም ህክምና ኮሌጅ ስልጠና ላይ በነበሩበት ወቅት እንደጀመሩት የተናገሩት ዶ/ር ታከለ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በተቆራረጠ ሁኔታ አልፎ አልፎ ብቻ ይለግሱ እንደነበር አስታዉሰው ከዚያ ወዲህ በየአመቱ 4 ጊዜ ማለትም በየ3 ወሩ አንድም ጊዜ ሳያቋርጡ ሲለግሱ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ደም መለገስ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ሙሉ ጤነኛና ደስተኛ መሆናቸውንና በቀጣይም ሳያቋርጡ በመለገስ በደም እጦት የሚጠፋውን ክቡር የሰው ህይወት ለመታደግ በጎ ተግባራቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
ደምን የሚተካ ሰው ሰራሽ ህክምና የለም ያሉት ዶ/ር ታከለ፤ በዚሁ ተግባር ዙሪያ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለውን የግንዛቤ ክፍተት ለማሻሻል ሚዲያን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በሙያቸው በጤና ተቋማት ውስጥ በሚያገለግሉበት ወቅት እንደ አሁኑ የተደራጀ ደምና ህብረ-ሕዋስ ባንክ አገልግሎት በአቅራቢቸው ባለመኖሩ በደም እጥረት ለጉዳት የሚዳረጉ ታማሚዎች መኖራቸውን ነው ዶ/ር ታከለ የገለጹት፡፡
ከዚህም ባሻገር ደም መለገስ ለጤንነት ጠቃሚ መሆኑና የተለየ የኑሮ የአመጋገብና መሰል መስፈርቶች የማይፈልግ በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡
ዶ/ር ታከለ አስፈላጊውን የቀለምና የሙያ ትምህርት ተከታትለው በመንግስት መስሪያ ቤት ከ12 አመታት በላይ ከማገልገላቸውም ባሻገር ባለትዳርና የልጆች አባት ሲሆኑ በዚህ ሁሉ የሕይወት መስመር ላይ ከሚያገኟቸው ደስታዎች ደም በመለገሳቸው የሚሰማቸው የመንፈስ ርካታ የተለየና ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የቦንጋ ደም ባንክ ከመቋቋሙ በፊት ደም የሚመጣው ከጅማ እንደነበርና አሁን ላይ በቅርበት ይህ አገልግሎት መጀመሩ እናቶች በወሊድ፣ በተለያየ አደጋዎችና ህመም ደም ለሚስፈልጋቸው በነጻ ደም የሚገኝበት እድል መፈጠሩ ከፍተኛ አስተዋጽዖ መኖሩን ከነበራቸው የሥራ ልምድና አጋጣሚዎች ጋር በማነጻጸር ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ አሳምነዉ አትርሳዉ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ከበልግ እርሻ ሰብሎች 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ማቀዱን የቡርጂ ዞን ገለጸ
ወጣቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ የነገ ህይወቱ ተቀይሮ ለሀገር እንዲተርፍ ክህሎቱን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተገለጸ
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የትምህርት ግበዓት መሟላት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ