በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን አመካ ወረዳ በ120 ሚሊዮን ብር በመንግስት በጀት እየተገነባ ያለው የመሰኖ ፕሮጀክት ስራ 95 በመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን አመካ ወረዳ በ120 ሚሊዮን ብር በመንግስት በጀት እየተገነባ ያለው የመሰኖ ፕሮጀክት ስራ 95 በመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን አመካ ወረዳ በ120 ሚሊዮን ብር በመንግስት በጀት እየተገነባ ያለው የኤርቆዕሜ መስኖ ፕሮጀክት ግንባታ 95 በመቶ መጠናቀቁን የወረዳው አስተዳደር ገልጿል፡፡

በወረዳው ፎርቆሴ ቀበሌ በህብረተሰብ ተሳትፎ አንድ ጤና ኬላ ወደ ጤና ጣቢያ ለማሳደግ የንቅናቄ ስራዎች መጀመሩንም የወረዳው አስተዳደር ገልጿል።

የአመካ ወረዳ 16 ቀበሌያት እና 3 ታዳጊ ማዘጋጃ ቤቶች በአጠቃላይ 19 መዋቅሮችን በስሩ የያዛ ሲሆን እራሱን ችሎ በወረዳነት መዋቅር ከተደራጀ 6 ዓመታትን አስቆጥሯል።

በመሆኑም የአካባቢው የልማት መነቃቃት ከመዋቅሩ ዕድሜ አንጻር ተስፋ ሰጭና የሚበረታታ ነው።

ለዚህ የልማት ተሳትፎ እንቅስቃሴ የአካባቢው ህብረተሰብ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የተናገሩት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደገፋ ሎበንጎ፤ በወረዳው በፎርቆሴ ቀበሌ በ120 ሚሊዮን ብር የኤርቆዕሜ መስኖ ፕሮጀክት ግንባታና የአመካ መስኖ ፕሮጀክት ጥገና ስራ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመንግስት በጀት እየተገባደደ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት የግንባታው ደረጃ 95 ከመቶ መድረሱን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ ቀሪው የፕሮጀክቱ ግንባታ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ልማት እንደሚገባም አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቱ ወደ ልማት መግባት የአካባቢውን የምርት አቅም በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግም ባሻገር የወቅቱን የገበያ ሁኔታን ከማረጋጋት አንጻር የላቀ ሚና እንደሚጫወትም ነው ያስረዱት።

በሌላ በኩል የፎርቆሴ ቀበሌ ሞቃታማ አካባቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየጊዜው የወባ በሽታ በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ የጤና ችግር እያስከተለ ስለመሆኑ ያመለከቱት አቶ ደገፋ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚል ከዚህ ቀደም አንድ ጤና ኬላ የነበረውን የህክምና ማዕከል ወደ ጤና ጣቢያ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ስራውም የሚንቀሳቀሰው በህብረተሰብ ተሳትፎ እንደሆነ የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፤ ለዚህም የተቋቋመው ኮሚቴ የገቢ አካውንት ቁጥር በመክፈት ወደ ስራ የገባ ሲሆን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚኖሩ የአካባቢ ተወላጆች በንቃት እንዲሳተፉም እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም ከመንግስት ሠራተኞች ጀምሮ የአካባቢው አርሶአደሮች እንዲሁም በሁሉም ቦታ የሚኖሩ የአከባቢ ተወላጆች ለስራው መሳካት የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያሳሰቡት አቶ ደገፋ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ተጨማሪ መሰረተ ልማቶችን ተግባራዊ የማድረግ እንቅስቃሴ ትኩረት የተሰጠው እንደሆነም አንስተዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አያይዘውም የህብተሰቡን የንፁህ መጠጥ ዉሃ ፍላጎት ለማጣጣም በወረዳው ጊዳሻ ቀበሌ በመንግስት ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ተገንብቶ በጀነሬተር አማካይነት አገልግሎት ይሰጥ የነበረውን ውሃ ባለሀብቶችን በማስተባበር ከጀነሬተር ወደ ኤሌክትሪክ ለመለወጥ በቅርቡ የትራንስፎርመር ግዢ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን