በጎፋ ዞን ለኬንቾ ተፈናቃዮች የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ ያለዉን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ጉብኝት አካሄደ

በጎፋ ዞን ለኬንቾ ተፈናቃዮች የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ ያለዉን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ጉብኝት አካሄደ

ማህበሩ ለተጎጂዎች ሰበዓዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ከኢየሱስ ክርስቶስ የኋለኛዉ ቀን ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን የልማት ድርጅትን በማስተባበር መኖሪያ ቤቶችን በማስገንባት ላይ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እና አጋር አካላት በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝድ ቀበሌ ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም በተከሰተዉ የመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

ማህበሩ ለተፈናቃዮች በስሙ ከሚያደርገዉ የቤት ግንባታ በተጨማሪ የኢየሱስ ክርስቶስ የኋለኛዉ ቀን ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር ለተፈናቃዮች በመገንባት ላይ ያሉ ቤቶችን የድርጅቱ ተወካዮችን በተገኙበት ጉብኝት ተደርጓል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የላንድ ስላይድና ፕለድ አፕል ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፀጋዬ አበጋዝ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ የጉብኝቱ ዓላማ የኢየሱስ ክርስቶስ የኋለኛዉ ቀን ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን የልማት ድርጅት ድጋፍ እየተገነቡ ያሉ ቤቶችና ተያያዥ ሥራዎችን በመመልከት ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከድርጅቱ ተወካዮች ጋር መረጃ ለመለዋወጥ ነዉ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከአለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ እንዲሁም ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን በጎፋ ዞን ኬንቾን ጨምሮ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሰዉ ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የዕለት ደራሽ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር መልሶ የማቋቋሙ ሥራ ላይ አሻራውን በማኖር ላይ መሆኑን አቶ ፀጋዬ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይና የፕሮጀክቱ ፕሮግራም ማናጀር የሆኑት አቶ ሮቤል ኦርሳንጎ በበኩላቸው፤ ቀይ መስቀል አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለተጎጂዎች በአይነት እና በገንዘብ ከ2 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የኋለኛዉ ቀን ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን የልማት ድርጅት እና መሰል ድርጅቶች ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ከቀይ መስቀል ጋር በመተባበር እየሰሩ ናቸዉ ብለዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የኋለኛዉ ቀን ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን የልማት ድርጅት እስከአሁን የ72 ቤቶች ግንባታ መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ ሳይት መሀንዲስ ኢንጂነር ናታን ዳዊት ገልፀዋል።

የፕሮጀክቱን ቀሪ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለማጠናቀቅ እየተፋጠነ ይገኛል ብለዋል ኢንጂነር ናታን።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጎፋ ዞን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ጣሰዉ፤ የኢየሱስ ክርስቶስ የኋለኛዉ ቀን ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን የልማት ድርጅት ለተፈናቃዮች የቤት፣ ሽንት ቤትና የውሃ ተቋማት ግንባታ በማከናወን ላይ ነዉ ብለዋል።

መንግስት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገዉን ጥረት የኢየሱስ ክርስቶስ የኋለኛዉ ቀን ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን የልማት ድርጅት በመደገፍ አጋርነቱን ማሳየቱን አቶ ኢያሱ ተናግረዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የኋለኛዉ ቀን ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን የልማት ድርጅት ተወካዮች በድርጅቱ ድጋፍ እየተሰሩ ያሉ ቤቶችን፣ የዉሃ ተቋማትና የሽንት ቤት ግንባታ ሂደትን በመመልከት ተጎጂዎችን አበረታተዋል።

ዘጋቢ: መንግሥቱ ታሪኩ – ከሳዉላ ጣቢያችን