የአርብቶ አደር አካባቢ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጤና በዘላቂነት ለማስጠበቅ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ

የአርብቶ አደር አካባቢ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጤና በዘላቂነት ለማስጠበቅ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ

የቢሮው ስራ ኃላፊዎችና በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ካንትሪ ዳይሬክተር አቢበኮ ካፖ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን የቱርሚ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ጥሩ ነገር እንደተመለከቱ የገለፁት በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ካንትሪ ዳይሬክተር አቢበኮ ካፖ (ዶ/ር) በሆስፒታሉ ለተኝቶ ታካሚ ተብሎ እየተሠራ ባለው ክፍል አካባቢ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በቆይታቸው የቱሪሚ ጤና ጣቢያ ነፍሰ ጡር እናቶች ማቆያን የተመለከቱ ሲሆን በዘርፉ የተጀመረው ስራ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ እንደገለፁት፤ በክልሉ የ90 ቀናት እቅድ ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ታቅደው እየተሠሩ ካሉት አንዱ የቱርሚ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሲሆን አሁን ላይ አጠቃላይ ግንባታው ከ90 በመቶ በላይ ደርሷል።

እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም ድረስ ቀሪ ስራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ የገለፁት ኃላፊው፤ ሆስፒታሉ ሲጠናቀቅ በዞኑ ከሐመር፣ ዳስነችና ኛንጋቶም ማህበረሰብ በተጨማሪ የጎረቤት ሀገር ኬኒያና ደቡብ ሱዳን ማህበረሰብንም ተደራሽ የሚያደርግ በመሆኑ የክልሉን ህዝብ ፍትሐዊ የጤና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የቱርሚ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ተቋራጭ የናታሊያ ኮንስትራክሽን ሳይት ኢንጂነር ሸምሱ ይማም፤ ግንባታው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ጨርሶ ለማስረከብ እየተሠራ እንዳለ ገልፀዋል።

በተያያዘ በዞኑ ለነፍሰጡ እናቶች በጤና ጣቢያ ማቆያ ተዘጋጅቶ እየተደረገ ያለው ሙያዊ ድጋፍ የምበረታታ ነው ያሉት አቶ እንደሻው በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች ተግባሩ በጥሩ ሁኔታ እየተመራ ይገኛል።

ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን