በደን ዙሪያ የወጡ ሕግና ደምቦች የብዝሃ ሕይወትን ሕልውና ከማስጠበቅ አንጻር ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደን ዙሪያ የወጡ ሕግና ደምቦች የብዝሃ ሕይወትን ሕልውና ከማስጠበቅ አንጻር ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ አስታውቋል፡፡

በተፈጥሮ ሐብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ አርአያነት ያላቸው አካላት ሊበረታቱ እንደሚገባም የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር አስራት ገ/ማሪያም(ዶ/ር) ገልጸዋል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ አቶ ንጉሴ ወ/ጊዮርግስ እንደገለጹት፤ መረጃዎችን ከመሰብሰብ ጀምሮ የወጡ ሕጎችና ደምቦች የደንና ብዝሃ ሕይወትን ሕልውና ከማስጠበቅ አኳያ የመተግበር ኃላፊነት ከሁሉም ይጠበቃል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት፤ ተቋሙ መቋቋሙን ተከትሎ ደምቦች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።

በደን ዙሪያ የወጡ ሕጎችና ደምቦችን ሥራ ላይ ለማዋል የሚደረገው ጥረት የደን ውድመትን ከመከላከል ባለፈ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

የናቡ ኢትዮጵያ ዓላማ ከሕብረተሰቡ የኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብር ጋር የደን ልማት ሥራዎችን አቀናጅቶ መምራት ነው ያሉት የናቡ ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ አሳየ አለማየሁ፤ በደን ልማት እና እንክብካቤ ዙሪያ የወጡ ሕጎች እንዲከበሩ በአፈጻጸም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን የማረምና የማስተካከል ሃላፊነት ከፍትህ አካላትና ከመላው ህብረተሰብ ይጠበቃል ብለዋል።

የካፋ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አጥናፉ አባተ እና ሌሎችም በጋራ እንደገለጹት፤ የደን ጉዳይ ለሰው ልጆችና ለብዝሃ ሕይወት ሕልውና አበርክቶው የላቀ በመሆኑ የወጡ ሕጎችን የመተግበሩ ሃላፊነት ለሌላው አካል የሚገፋ ባለመሆኑ ተቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከደን ሐብት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የቀረቡትን ደምቦች ሥራ ላይ ከማዋል አንጻር የድጋፍና የክትትል ሥራዎች ተጠናክረው የሚሰሩ መሆናቸውን የገለጹት የደን አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊው ኢንጂነር አስራት ገ/ማሪያም(ዶ/ር)፤ በደን አጠባበቅ ዙሪያም ሕጋዊ ፈቃድ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የካርበን ሽያጭ ተጠቃሚ ለመሆን መረጃዎችን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው፤ የደን ውሳኔዎችን ከማሳካት አኳያ የወንጀልና የፍታብሔር ክሶችን ተፈጻሚ ማድረግ የደን ውድመትን ለመከላከል አስተዋጽዖው የጎላ ነው ብለዋል።

በተፈጥሮ ሐብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ተከታትሎ በሕግ እንዲከበር ከመከወን አንጻር አርአያነት ያለውን ተግባር የፈጸሙ በካፋ ዞን የዴቻ ወረዳ የሞዲዮ ያቻ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ እራጎ ወ/ሚካኤል የዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ፡ መለሠ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን