በህዝብ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ እየቀረበ ያለውን የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄ በተግባር ለመመለስ እየሠራ መሆኑን የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በህዝብ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ እየቀረበ ያለውን የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄ በተግባር ለመመለስ እየሠራ መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር ገልጿል፡፡

አስተዳደሩ ይህንን ያለው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን በወረዳው 9 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አዳሜ-ቡዱክሳ የገጠር መንገድ ጥገና ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በተካሄደበት ወቅት ነው።

የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ እየተሠሩና እየተጠገኑ ያሉ መንገዶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ከመቅረፍ ባለፈ ህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የይርጋጨፌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ በቀለ፤ በህዝብ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ እየቀረበ ያለውን የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በተግባር ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በወረዳው በዘንድሮ በጀት ዓመቱ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር መገንድ አዳዲስ ከፈታና ጥገና እንደሚደረግ ምክትል አስተዳዳሪው ጠቁመው ከሚጠገኑት መካከል ከአዳሜ እስከ ቡዱክሳ ቀበሌ 9 ነጠብ 6 ኪሎ ሜትር እና ከይርጋጨፌ እስከ ሰዴ 7 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ የጥገና ሥራ፣ ከሐራንጃ-ዶማርሶ እስከ ቱቲት ቀበሌ 18 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ ከፈታ እና የቱሊሴና ቆንጋ ድልድዮች ግንባታ ለማስጀመር መታቀዱን አስረድተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን የዲላ ዲስትሪክት አስተባባሪ አቶ ፍሰሐየሱስ ካሳዬ በበኩላቸው፤ በዞኑ ጥገና የሚያስፈልጋቸው የገጠር መንገዶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመለየት እየሠሩ እንደሆነ ገልፀው፤ ተግባራት በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘብዴዎስ ኤካ፤ ከኢትዮጵያ መንዶች ባለሥልጣን ጋር በመሆን በክልሉ በተለያዩ ዞኖች የገጠር መንገድ ጥገናና ከፈታ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ ከ3 መቶ 20 ኪሎ ሜትር በላይ የአዳዲስ መንገድ ከፈታና ከ1 መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ጥገና እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ኢንጂነር ዘብዴዎስ፤ ኅብረተሰቡ በሥራው ከሚያደርገው ተሳትፎ ባለፈ የተሠሩና የተጠገኑ መንገዶች በመጠበቅና በማስጠበቅ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ካነጋገርናቸው ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል አቶ ዳዊት ሹጥዮ እና አቶ ሳሙኤል አሰፋ በሰጡት አስተያየት፤ የመንገዱ ጥገና በአካባቢያቸው እየተመረቱ ያሉ የቡናን ምርት ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በቀላሉ ወደ ከተማ ለማድረስ እንደሚያግዛቸው በመግለፅ ሥራው በመጀመሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም እየተሠሩና እየተጠገኑ ያሉ መንገዶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ከመቅረፍ ባለፈ ህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን