በጎ ፈቃደኞች በዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባባት ስራ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማኖር የገቡትን ዓላማ በማሳካት አብሮነት እንዲጎለብት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የኢፌዲሪ ሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ

በጎ ፈቃደኞች በዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባባት ስራ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማኖር የገቡትን ዓላማ በማሳካት አብሮነት እንዲጎለብት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የኢፌዲሪ ሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የ12ኛ ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠና ማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል እና የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ ወ/ሮ አስቴር በሽር ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ ዜጎች በጎነት የመንፈስና ህሊና እርካታ የሚሰጥ የተቀደሰና የተባረከ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።

ሰላም ሚኒስቴር በአገሪቱ ከዳር እስከ ዳር ያሉትን ወጣቶች በማቀናጀት በበጎ ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ የሕዝቦች አብሮነትና አንድነት የበለጠ እየጎለበተ እንደሆነም ወ/ሮ አስቴር አክለዋል።

በጎ ፈቃደኞች በዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባባት ስራ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማኖር የገቡትን ዓላማ በማሳካት አብሮነት እንዲጎለብት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።

በአንድነት፣ በወንድማማችነት እና በአብሮነት ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ የሀገር ግንባታ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጎልበት ያደገና የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚቻልም ወ/ሮ አስቴር አስገንዝበዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ኤርሚያስ ሞሊቶ(ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን ሰላምና አብሮነት ለማጎልበት በበጎ ፈቃደኝነት የተሰማሩ ወጣቶችን የማሰልጠን ዕድል አግኝቶ ላለፉት በርካታ አመታት አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው የሰላም ዋጋ አይተኬ መሆኑን በመረዳት እንደሆነ ተናግረዋል።

ተቋሙ ተግባሩን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በበጎ ፈቃድ የማሕበረሰብ አገልግሎት ላይ የተሠማሩ በጎ ፈቃዳኛ ወጣቶች ኢትዮጵያዊ እሴቶች እና መርሆዎች ለትውልድ እንዲተላለፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ለመሳተፍ ስልጠና ወስደው የተመረቁ አንዳንድ ተመራቂዎች በበኩላቸው በጎነት ለራስ መሆኑን በመገንዘብ ለአገራቸው ሰላምና አብሮነት የድርሻቸውን ለመወጣት ወደ ተግባሩ መሰማራታቸውን አውስተዋል።

የሰላም ሚኒስቴር እና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ባለድርሻ አካላት በፕሮግራሙ ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን