ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

ሀዋሳ: መጋቢት 14/2017 (ደሬቴድ) ኢትዮጵያ ላለፉት 3 ቀናት በቻይና ናይንጂንግ ከተማ ሲካሄድ በቆየው በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 3ኛ ደረጃን በመያዝ ተሳትፎዋን አጠናቃለች።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 2 የወርቅ እና 3 የብር ሜዳልያ በድምሩ 5 ሜዳልያዎችን በማግኘት ከአሜሪካ እና ኖርዌይ በመቀጠል ከዓለም 3ኛ ደረጃን ስትይዝ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች።

2 የወርቅ ሜዳልያዎች በሴቶች 3 ሺህ ሜትር በአትሌት ፍሬወይኒ ሀይሉ እና በሴቶች 1500 ሜትር በአትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ አማካኝነት መገኘታቸው ይታወቃል።

3ቱ የብር ሜዳልያዎች ደግሞ በወንዶች 3 ሺህ ሜትር በአትሌት በሪሁ አረጋዊ፣በሴቶች 1500 ሜትር በአትሌት ድርቤ ወልተጂ እና በሴቶች 800 ሜትር በአትሌት ንግስት ጌታቸው አማካኝነት ተገኝተዋል።

አሜሪካ በ6 የወርቅ፣በ4 የብር እና በ6 የነሃስ ሜዳልያዎች በድምሩ 16 ሜዳልያዎችን በማግኘት ከዓለም ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ ኖርዌይ በ3 የወርቅ እና በ1 የነሃስ ሜዳልያ በድምሩ 4 ሜዳልያዎችን በማግኘት 2ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

21ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በፖላንድ ቱራንድ ከተማ በቀጣይ ዓመት መጋቢት ወር 2018 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ