የቲቢ በሽታን ለመቆጣጠር በቅንጅት መሠራት እንደሚገባ ተጠቆመ

የቲቢ በሽታን ለመቆጣጠር በቅንጅት መሠራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ: መጋቢት 14/2017 (ደሬቴድ) የቲቢ በሽታን ለመቆጣጠር በቅንጅት መሠራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአርባ ምንጭ ሲከበር የቆየው 19ኛው አመታዊ የቲቢ በሽታ ምርምር ጉባኤና የ2017 ዓ.ም. የዓለም የቲቢ በሽታ ቀን በእግር ጉዞ ተጠናቋል።

በየማጠቃለያ መድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ስራ ዶ/ር ህይወት ሰለሞን የሳንባ ነቀርሳ በአለም ላይ ከፍተኛ የጤና መታወክ እያስከተለ በመሆኑ ለመቆጣጠር በቅንጅት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በበሽታው በየዓመቱ በርካታ ሰዎች እንደሚሞቱ ገልጸው በተለይም መድሀኒት የተላመደ ቲቢ እየተስፋፋ በመሆኑ የግንዛቤ ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲሰራ ዶ/ር ሕይወት አሳስበዋል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ተክሉ ወጋየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሽታውን ለመከላከል በቂ አቅም ያለን በመሆኑ ከቲቢ ነጻ ሕብረተሰብ ለመፍጠር መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።

የቲቢ ቀን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንዲያዘጋጅ ዕድል በመሰጠቱ ዶ/ር ተክሉ አመሥግነዋል።

በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየተሰሩ ያሉ ጥናቶችና ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር የቲቢ በሽታ የአለም ጤና ስጋት እንዳይሆን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል እና የፕሮግራሞች ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ በበኩላቸው የቲቢ ሕሙማን ልየታ እና ሕክምና አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ በመስጠት በክልሉ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸው በሽታውን ይበልጥ ለመግታት አሁንም የግንዛቤ ሥራ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ ቲቢን ለመከላከል ብሎም አክሞ በማዳን ምሣሌ የሆኑ የጤና ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ልምዳቸው ያካፈሉ ሲሆን የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ለሶስት ተከታታይ ቀናት ” በርግጥም ቲቢን መግታት እንችላለን፤ ቃል በተግባር ሐብት ለውጤት ” በሚል መሪ ቃል ‎ሲከበር የቆየው የዓለም የቲቢ ቀን በእግር ጉዞ እና በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ተከብሮ ውሏል።

ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን