በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መልዕክቶችን ከመቀበልና ከማጋራት አስቀድሞ ተዓማኒነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ

በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መልዕክቶችን ከመቀበልና ከማጋራት አስቀድሞ ተዓማኒነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ: መጋቢት 14/2017 (ደሬቴድ) ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መልዕክቶችን ከመቀበልና ከማጋራት አስቀድሞ ተዓማኒነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ የትምህርትና የህግ ዘርፍ አካላት ገለጹ።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ ሀሰተኛ መልዕክቶች መበራከት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያስከተለ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ተማሪ አማኑኤል ሰለሞን እና ኤቢሴ ታምሩ በዋቸሞ ዩንቨርሲቲ የመጀመሪያ አመት ተማሪዎች ሲሆኑ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ሀሰተኛ መልዕክቶች የማህበረሰቡን በሠላም የመኖር ዕሴቶችን በመሸርሸር እርስ በእርስ እንዲጠራጠርና እንዲንጋጭ እያደረገ ነው ብለዋል።

በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ አብዛኛው ተማሪ በሚባል ደረጀ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ በመሆኑ ቴክኖሎጂው ይዞት የመጣው የአሠራር ማቅለያ ዘዴ ተማሪዎች መሠረታዊ ዕውቀትን በአግባቡ እንዳይጨብጡ እያደረጋቸው ነው የሚሉት ተማሪዎቹ፥ የማህበራዊ ሚዲያ የአጠቃቀም ስረዓታችን ጤናማና በጎ ዓላማን ትኩረት ያደረገ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በማህበረሰቡ ውስጥ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ የጥላቻ ንግግሮችንና የመሳሰሉ ጎጂ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶችን በማስቀረት በአንጻሩ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ባህላችንና መልካም ዕሴቶቻንን ለቀሪው አለም ለማስተዋወቅ እንዲሁም አንድነታችንን ለማጠናከር መጠቀም ብንችል የተሻለ ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በዩንቨርሲቲው በፖለቲካና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል የሠላምና ግጭት ጥናት መምህር ጌታሁን አበራ በኩላቸው፥ ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መልዕክቶችን ከመቀበልና ከማጋራት አስቀድሞ ተዓማኒነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ ሀሰተኛ መልዕክቶች የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ኪሳራ በቀላሉ መጠገን የሚከብድ ነው የሚሉት መምህር ጌታሁን፥ ዛሬ ላይ ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን ሲውል ሲያድር ከግለሰቦች መበጣበጥ እስከ ሀገር መፍረስ ሊያደርስ የሚችል ተግባር በመሆኑ የጥንቃቄ አከሄዶችን ከወዲሁ ማበጀት አማራጭ የሌለ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በዚህ አይነት እኩይ ተግባር ላይ በመሳተፍ ምትክ የሌላትን ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ባልተገባ ግጭት ውስጥ የሚከቱ አካላት ቆም ብሎ ነገን ማሰብ ቢችሉ የተሻለ እንደሆነም ጠቁመዋል::

መምህር ጌታሁን አክለውም ፀፀት አስቀድሞ የሚመጣ ክስተት ባለመሆኑ ሁሉን ነገር በስክነትና በአርቆ አሳቢነት እንዲሁም የሚስተዋሉ የሀሳብ ልዩነቶችን ቢቻል ፊት ለፊት በመወያየት ለሀገር ሠላምና ዕድገት በጋራ መቆም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡት የህግ አማካሪና ጠበቃ እንዲሁም በወራቤ ዩንቨርስቲ የህግ መምህር አቤኔዘር ሳሙኤል በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ ሀሰተኛ መልዕክቶችንና የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል የተቀመጠ የህግ ድንጋጌ ስለመኖሩ በማመላከት ሆኖም ወንጀሉ ተፈፅሞ ሲገኝ እንደወንጀሉ አይነት ከ100ሺህ የብር ቅጣት እስከ አምስት አመት በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ እንደሚችል ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህንኑ ተከትሎ የሰው ሕይወት ጠፍቶ ከሆነ ደግሞ የቅጣት መጠኑ በወንጀል ህጉ በተቀመጠው መሠረት በነፍስ ግዲያ ወንጀል ሊያስጠይቅ ይችላል የሚሉት የህግ ባለሙያው ችግሩን ለመቅረፍ በዋናነት የህግ ስርዓት መጠናከር፣ የማህበረሰቡ የንቃተ ህሊና ደረጃ ማደግና የአጠቃቀም ስረዓቱ አመክንዮአዊ መሆን ወሳኝ እንደሆነም አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን