ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ እና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የተቋማት አደረጃጀት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለህብረተሰቡ በቅርበት ቀልጣፋ እና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የተቋማት አደረጃጀት ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።

በሚዛን አማን ከተማ ለክልል ተቋማት ቢሮ ግንባታ የሚውል በ2ሺ 600 ካሬ ላይ የሚያርፍ ባለ ሰባት ወለል ህንጻ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠለት።

በቅርቡ የክልሉ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ በአራቱ ከተሞች የርእሰ መስተዳደሩን ቢሮ ጨምሮ አራት የክልል ተቋማቶችን በ5 ነጥብ 763 ቢሊየን ብር ለማስገንባት ከተለያዩ ተቋራጮች ጋር የውል ስምምነት መፈጸሙ ተመላክቷል፡፡

የክልሉ መንግስት በብዝሃ ዋና ከተሞች ለቢሮ ሥራ አገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎችን ለማከናወን ከሦስት የተለያዩ የግንባታ ሥራ ተቋራጮች ጋር የውል ስምምነት የፈጸመ ሲሆን፥ ግንባታውን በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ግብ ተጥሎ እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡

የህንጻ ግንባታው የክልል ተቋማቱን የቢሮ እጥረት ከመቅረፍ ባሻገር ህብረተሰቡ በቅርበት የተሻለና ቀልጣፋ ምቹ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኝም ያስችላል ተብሏል።

የዚሁ ህንጻ ግንባታ አንዱ አካል የሆነው እና በክልሉ ከሚገኙ ብዙሀን ከተሞች አንዷ በሆነችው በሚዛን አማን ከተማ ለክልል ተቋማት ቢሮ አገልግሎት የሚሰጥ ባለ ሰባት ወለል ህንጻ በ2 ሺ 600 ካሬ ላይ የሚያርፍ ህንጻ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለታል።

በስነ ስረአቱ ላይ ተገኝተው የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደተናገሩት፥ የክልል ምስረታችን ዋንኛ አላማው ህብረተሰቡ መሰረታዊ የህዝብ ፍላጎትና ጥያቄዎችን በቅርበት ለመፍታት ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ በቅርበት መገንባትና ማስተዳደር ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በሚዛን ማዕከል የክልል ተቋማት ቢሮ ህንጻ ይገነባል ብለዋል። ህንጻው የክልል ተቋማትን ወደ አንድ ማዕከል የሚሰበስብና ዘመናዊና ቀልጣፋ እና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ያመቻል ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በበኩላቸው፥ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እንደ ህዝብ ከተጎናፀፍናቸው ድልና ብስራት አንዱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምስረታ አንዱና ተጠቃሹ ነው ብለዋል። በከተማው ርዕሰ መስተዳድሩ በአካል ተገኝተው ለቢሮ ግንባታው የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸው ለመላው ህዝባችን ትልቅ ኩራትና ክብር ነው ብለዋል።

የህንጻው መገንባት የክልል ተቋማት ፈጣን፣ ምቹ፣ ቀልጣፋና ለተገልጋዮች እርካታን በሚጨምር መልኩ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ለከተማችን ተጨማሪ ውበትና ድምቀትን የሚጨምር መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የዞኑ መንግስት የህንጻው ግንባታ እስኪጠናቀቅ ያላለሰለሰ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ ባሻገር ሁሉ አቀፍ ትብብር ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል ።

በመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርዓት ላይ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን