የአርብቶ አደሩን የምጣኔ ሀብት አቅም ለማሳደግና ኑሮአቸዉን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርብቶ አደሩን የምጣኔ ሀብት አቅም ለማሳደግና ኑሮአቸዉን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በቅንጅት እያከናወነ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ጂ አይ ዜድ ኢትዮጵያ የተሰኘ ፕሮጀክት የተጎዱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የአርብቶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የ2 ሚሊየን ዩሮ በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊና የአርብቶ አደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ አይዴ ሎሞዶ እንደገለፁት፤ አርብቶ አደሩ ከእንስሳት እርባታው ባሻገር በተለያዩ የስራ መስኮች በህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተው የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ ጂ አይ ዜድ ኢትዮጵያ ከተሰኘ ፕሮጀክት ጋር በማተባበር በክልሉ ሶስት ወረዳዎች በበናፀማይ ሀመርና ኛንጋቶም ወረዳ አራት የህብረት ስራ ማህበራትን በማደራጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።

የጂ አይ ዜድ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ማይክ ባርተልስ በበኩላቸው፤ የተጎዱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት ከተራራ የሚወርዱ የጎርፍ ውሃዎችን በመገደብ የአየር ንብረት ለዉጥን በመቋቋም የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

አክለውም ይህንን ፕሮጀክት ለማስፈፀም የ2 ሚሊየን ዩሮ በጀት የተመደበ ሲሆን የአርብቶ አደሩ ተጠቃሚነት ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በጂ አይ ዜድ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ድርቅን የመቋቋም አቅም ግንባታ ፕሮጀክት የኦሮሚያና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ኮምፖነንት ማናጀር አቶ መስፍን ብርሃኑ፤ በሚሰራው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አርብቶ አደሩ በህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተው የገቢ አቅማቸውን በማጎልበት መሬታቸዉን ወደ ምርታማነት እንዲቀይሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለተደራጁ አራት ማህበራት ለእያንዳንዳቸው የአንድ ሚሊየን ብር የድጋፍ ስምምነት መፈፀሙን ገልፀዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ አረጋ፤ አርብቶ አደሩ በተመረጡ ቦታዎች ላይ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የራሳቸውን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ለማድረግ ፕሮጀክቱ ከመንግስት ጋር በመተባበር በሚሰራው ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመቀናጀት አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

የአካባቢዉ አርብቶ አደሮች በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የተፈጥሮ ሀብቶችን በመጠበቅና በማልማት ኢኮኖሚያቸውን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል በጂ አይ ዜድ ፕሮጀክት በኩል የግንዛቤ ስልጠና እና የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውን ገልፀው በተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ በተደራጁበት የስራ መስክ ተቀናጅተዉ በመሥራት የሚጠበቅባቸዉን ለዉጥ ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን