የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ ለማስተሳሰር ከሰንበት እስከ ሰንበት ገበያ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለጸ

በወልቂጤ ከተማ ጉብሬ እና በኩር ክፍለ ከተሞች የሰንበት ገበያዎች የማስጀመሪያ ስነ-ስርአት ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ብርሀኔ እንዳሉት፤ የሰንበት ገበያ እንደሀገር የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ አንስተው የአርሶአደሩ ምርት እንዲዳረስና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል።

በዞኑ 29 የሰንበት ገበያዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ በእነዚህም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

ከሰንበት እስከ ሰንበት ገበያ ገበያውን ከማረጋጋት ባሻገር ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን ለመምራት ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

አያይዘውም የሰንበት ገበያ የምግብ ምርቶች ያለደላላ ጣልቃ ገብነት አምራቹን በቀጥታ ከሸማቹ ጋር በማገናኘት ለገበያው አቅርቦ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸምትበት ሲሆን ዋጋ ጨምረው በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ህግ የማስከበር ስራ እንደሚሰሩ አቶ መላኩ አመላክተዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት አመት በከተማ አስተዳደሩ አምራቹና ሸማቹ በቀጥታ የሚገበያዩበት የግብይት ማዕከላትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

እንደ ወልቂጤ ከተማ ከዚህ ቀደም ሁለት የሰንበት ገበያዎች የተቋቋሙ ሲሆን በተጨማሪም የጥምቀተ ባህርና በጉብሬ ክፍለ ከተማ ሰንበት ገበያው ከመደበኛ ገበያው በተሻለ ዋጋ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረብ ችለዋል፡፡

የወልቂጤ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብድልከሪም መሀመድ፤ በክፍለ ከተማው ለንግድ የሚሆኑ ሼዶች ተገንብተው ወደ ስራ መገባቱን አንስተው ለቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በተለይም ማህበረሰቡ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን እንዲቆጥብ እንዲሁም ሼዶችን በመስራት ከፀሀይና ዝናብ ለመከላከል በሚያስችል መልኩ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ነጋዴዎቹ ከመደበኛው የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ባለሙያ በመመደብ የክትትል ስራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በሰንበት ገበያ ሲገበያዩ ያገኘናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፤ ከሰንበት እስከ ሰንበት ገበያ በቅርበት በመኖሩና የንግድ ቦታ ሼዶችን በመሰራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ነጋዴዎቹ በበኩላቸው ገበያውን በቅርበት በማግኘታቸው የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርቡ አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ ዝናሽ ሙሉጌታ – ከወልቂጤ ጣቢያችን