ኢትዮጵያዊያን የሚለያዩ ነገሮችን በመተው አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ከቻሉ የትኛውንም ነገር መስራት እንደሚቻል ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማሳያ መሆኑ ተገለጸ

ኢትዮጵያዊያን የሚለያዩ ነገሮችን በመተው አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ከቻሉ የትኛውንም ነገር መስራት እንደሚቻል ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማሳያ መሆኑ ተገለጸ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የዞን እና የልዩ ወረዳ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የ14ኛ ዓመት ክብረ በዓል አከባበር ግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ አሼቦ የ14ኛ ዓመት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የክብረ በዓል አከባበርን አስመልክቶ በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመድረኩ ዋና አላማ ባለፉት ዓመታት ህዝቡ ለግንባታው ባደረገው አስተዋጽኦ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመጨበጥ በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ለመምከር መሆኑን ገልጸዋል።

ለግድቡ ግንባታ እንደሀገር ባለፉት 14 ዓመታት በህብረተሰብ ተሳትፎ 21.6 ቢልየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 420 ሚሊዮን ብር በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሰብሰብ መቻሉንም አቶ ተክሌ ገልጸዋል።

በተለይ ህብረተሰቡ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ የንቅናቄ ስራዎችን ባለፉት14 ዓመታት መስራት መቻሉን አቶ ተክሌ ጠቅሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መላ ኢትዮጵያዊያንን ያስተሳሰረና ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደምትችል ማሳያ መሆኑንም አቶ ተክሌ ተናግረዋል።

14ኛው ዓመት ክብረ በዓል ሲከበርም እስከአሁን ላደረገው አስተዋጽኦ ህብረተሰቡ ሊመሰገን ይገባል ያሉት ኃላፊዉ፤ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የህዳሴ ግድብ የህብረተሰብ ተሳትፎ የተመራበትን ሂደት በሰነድ መልክ ለትውልድ ማስቀመጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በቀጣይ በክልል ተቋማት የቦንድ ሽያጭ መድረኮች እንደሚዘጋጅና የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል የማጠናከር ስራ ተጠናክሮ እንደሚሰራም ተገልጿል።

ኢትዮጵያዊያን የሚለያዩ ነገሮችን በመተው አንድነትን በሚያጠናከሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ካደረግን የትኛውንም ነገር መስራት እንደምንችል ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማሳያ መሆኑን አንዳንድ የመድረኩ ተሳታፊዎች አንሰተዋል።

14ኛዉ ዓመት በሚከበርበት ወቅትም ድጋፍ ያደረጉ አካላትን በማመስገን እና የቦንድ ሽያጭ በማካሄድ እንደሆነም አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የዓሣ ምርት መስጠት የጀመረ ሲሆን የሀገር ውስጥ የሃይል ክፍተትን በመሙላት ለዉጭ ገበያ በማቅረብ እንዲሁም በመስኖና በቱሪዝም ልማት ዘርፍም ለሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ተብሏል።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሣዕና ጣቢያችን