ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ ሁለት የሠርግ ሥነ ስርዓታቸውን ለፈጸሙ ጥንዶች የእንኳን ደስአላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ዛሬ በተመረቀው በወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ ሁለት የጥንዶች የሠርግ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቻ ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ ሁለትን በከፈትንበት ዕለት በሠርግ ዐጸዱ ጋብቻችሁን የፈጸማችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጋብቻ የሀገር መሠረት ከሆኑት ተቋማት አንዱ የሆነው ቤተሰብ የሚመሠረትበት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

አክለውም÷ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን፣ ሌሎችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ዓለም አቀፍ፣ ሀገራዊ እና ማኅበራዊ ክንውኖች የሚፈጸሙበትን ድንቅ ስፍራ በሠርጋችሁ ደስታ አድምቃችሁ አስጀምራችሁታል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እና ለስሟ የሚመጥን ገጽታ እንዲኖራት ታልሞ ሲሠራ የቆየው የወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ ሁለትዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ መከፈቱ ይታወቃል፡፡

የተለያዩ ሁነቶች የሚስተናገዱባቸውን ዘመናዊ አዳራሾችንና ማዕከላትን የያዘ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋብቻቸውን ለመፈጸም የተዘጋጁ ወይም አቅደው ሳይሳካላቸው የቆዩ ጥንዶችን በመሥፈርት መርጦ የጋብቻ ሥርዓታቸውን በዛሬው ዕለት የወዳጅነት የሠርግ ዐጸድ እንዲፈጽሙ አድርጓል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ እንዳመላከተው÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ ሁለት የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ከተሞሸሩ ጥንዶች ጋር ቆይታን አድርገዋል።

ምዕራፍ ሁለት መጠናቀቁን በማስመልከት ጋብቻቸውን በዕለቱ በሠርግ አጸዱ ለመፈጸም ለሚሹ ጥንዶች ለቀረበው ጥሪ ምላሽ የሰጡ ተሞሽረውበታል፡፡

አረንጓዴ ልማቱ ለብሔራዊና ማኅበራዊ ክንውኖች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን÷ በልዩ ልዩ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች መንፈስን የሚያድስ ጊዜ የሚያሳልፉበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፓርኩ ለመጪው አንድ ሣምንት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ተጠቁሟል፡፡

በአልዓዛር ታደለ