የዲጂታል ስማርት ክፍል ተማሪዎችን ከዘመኑ ጋር ለማስተሳሰርና ተጨማሪ ትምህርት ቀስመው ውጤታማ እንዲሆኑ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የወላይታ ዞን አረካ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት አስታወቀ
በክፍሉ ያሉ ኮምፒውተሮች በኔትወርክ የተገናኙና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳለም ተመላክቷል፡፡
በአረካ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ካነጋገርናቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ መርሁን ከበደ፣ ተማሪ ክርስቲያን ይስዕቅና ተማሪ መልካሟ ላንቤቦ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በዲጂታል ስማርት ክፍል የተለያዩ ማጣቀሻ መጻህፍትና በዩቲዩብ የተጫኑ ትምህርቶችን በመከታተል ውጤታማ መሆናቸውን ተናግርዋል፡፡
በዲጂታል ስማርት ክፍል ያሉ ኮምፒውተሮች በኔትወርክ የተገናኙና የኢንተርኔት አገልግሎት ስለአለ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተሻሉ ትምህርቶችን እያገኙ እንዳሉ ያነሱት ተማሪዎቹ፤ ኮምፒውተሮች ቁጥር ከተማሪዎች ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ኮምፒውተሮች እንዲጨመሩ ጠይቀዋል።
በዲጂታል ስማርት ክፍል አንዳንድ ትምህርቶችን ኦን ላይን(Online) ፈተና እየወሰዱ ለመጪው ሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጅት እያደረጉ እንዳለም ተናግረዋል።
በአረካ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዲጂታል ስማርት ክፍል አስተባባሪና የኮምፒውተር መምህር ጋሬዶ ባልጎ፤ ተማሪዎች ዲጂታል ስማርት ክፍል በፈረቃ እንዲጠቀሙና ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ እንዳለ አስረድተዋል።
ተማሪዎች ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲዘምኑና የኦን ላይን ፈተናዎችን እንዲለማመዱ ከማድረግ አኳያ ዲጂታል ስማርት ክፍል ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት በአረካ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አለማየሁ አድሎ፤ በትምህርት ቤቱ ዲጂታል ስማርት ክፍል፣ ኮምፒውተር ላብራቶሪ እና አይ ሲ ቲ (ICT) ክፍሎች በኮምፒውተር የተደራጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኮምፒውተር ቁጥር ለመጨመር ዕቅድ መያዙን ያነሱት ርዕሰ መምህሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ችግሩን ለመቅረፍ ጅምር ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
የአረካ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደነቀ ኡንቻሬ በበኩላቸው፤ በከተማው ካሉት ሦስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአረካ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዲጂታል ስማርት ክፍል መጀመሩን አንስተው፤ ተማሪዎችን ከዘመኑ ጋር ለማስተሳሰርና ተጨማሪ ትምህርት ቀስመው ውጤታማ እንዲሆኑ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቶ ውጤት ማስገኘቱን አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
በመላው ሀገሪቱ በቀጣይ ጊዜያት 50 ሞዴል ትምህርት ቤቶች ለመገንባት እየተሰራ ነው መሆኑን የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ
ተወዳዳሪ ዜጋ እንድትሆኑ ሳትሰርቁ ጠንክራችሁ ፈተናችሁን በራሳችሁ ሥሩ – ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)
በክልሉ እየተስተዋለ ያለው ህገ-ወጥ የህጻናት የጉልበት ብዝበዛና ፍልሰት ዘርፈ ብዙ ችግር እያስከተለ ነው -አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)