እንደሀገር ካለንበት ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ምክክሩ እንደሚያግዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ

እንደሀገር ካለንበት ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ምክክሩ እንደሚያግዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ12 የክልሉ ዞኖችና ከ96 ወረዳዎች ከ 10 ማህበራዊ መሠረቶች እየተሳተፉ ያሉት አካል ጉዳተኞች እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክሩ፣ አሁን ካለንበት  ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ያግዛል።

መምህር በላይ ባሳ በደቡብ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከወላይታ ዞን ተሳታፊ አካል ጉዳተኛ ናቸው። በውይይቱ በመሳተፋቸው ደስተኛ ስለመሆናቸው የገለጹት አካል ጉዳተኛው፣ ምክክሩ ሀገራችንን ወደምንፈልገው መልካም አቅጣጫ የሚመራት በመሆኑ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ለሀገራችን የሚጠቅማትን ሀሳብ በነጻነት ገልጸናል ያሉት መምህር በላይ፣ አሁን ካለንበት ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን መድረኩ የሚያግዝ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

መምህር አዲሱ ኢዮብ ከኮንሶ ዞን የተሳተፉ ሌላኛው አካል ጉዳተኛ ሲሆኑ፣ በምክክር ሂደቱ ሀሳባቸውን በነጻነት እያቀረቡ ስለመሆናቸውና ምክክሩ አዋጭ መሆኑን ገልጸው፣ በምክክሩ መነሻ ከተሰራ ሀገራችን ውጤታማ ትሆናለች ነው ያሉት።

የኔ የሚለውን ትተን እንደሀገር የጋራ ነገሮቻችን ላይ ከሰራን ለውጡ ይመጣልም ብለዋል።

ከጋሞ ዞን የተሳተፈችው መ/ርት መድኃኒት ይማም በበኩሏ ሀገራዊ ምክክሩ  ከዚህ በፊት የተለመደ ቢሆንና ችግሮች በንግግር ቢፈቱ ዋጋ አንከፍልም ነበር ብለው፣ በምክክሩ ችግሮች እንዲፈቱ አሻራችንን እያስቀመጥን ነው ብለዋል።

አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በሁሉም ማህበራዊ መሰረቶች የነበሩ ተሳትፎዎች አስደሳች እንደነበሩና ምክክሩ በተግባር ውጤት አምጥቶ ለማየት ጉጉት እንዳላቸውም አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን