የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መቀረፍ እንዳለባቸዉ ተመላከተ

የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መቀረፍ እንዳለባቸዉ ተመላከተ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መቀረፍ እንዳለባቸዉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን  እየተሰራ መሆኑን የልዩ ወረዳው መንገድና ትራንስፖርት  ልማት ጽ/ቤት ገልጿል።

በልዩ ወረዳው  ከትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች መካከል ወጣት ሹማቴ ፈረዳ እና መምህር መልካሙ አሰፋ በሰጡት አሰተያየት፤ ባለፉት ለተወሰኑ ጊዜያት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ መጠነኛ ለውጦች ታይተው የነበሩ ቢሆንም አሁን ላይ የተለያዩ ምክንያቶችን በመንገር ከታሪፍ በላይ የማስከፈልና መሠል ችግሮች እየተስተዋሉ በመሆኑ ጉዳዩ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ ጠይቀዋል።

አሁን ላይ በሀገራችን በሌሎች አከባቢዎች የተጀመረው ቴክኖሎጂ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ እንደ ልዩ ወረዳውም ይህ ተግባራዊ እንዲደረግ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሙዱላ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ ጽ/ቤት የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር ሂደት አስተባባሪ ረዳት ሳጂን ስንታየሁ መኩሪያ በበኩላቸው፤ ስራዎች እየተሠሩ ቢሆንም ለቁጥጥር የማይመቹና የምሳ ሰዓት ዓይነት ጊዜያትን በመጠቀም ትርፍ የማስከፈልና መሰል ችግሮች እየተስተዋሉ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት የልዩ ወረዳውና የከተማ አስተዳደሩ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በጋራ የምንሰራ ይሆናል ነው ያሉት።

የሙዱላ ከተማ አስተዳደር በኢኮኖሚ ክላስተር የትራንስፖርት ቡድን መሪ አቶ ላቀው ገ/ፃድቅ እንደተናገሩት፤ መኪናው ገና ከመናኸሪያ ሳይወጣ ጀምሮ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሰራ ያለ ቢሆንም የናፍጣ ጭማሪና መሰል ምክንያቶችን በመንገር ትርፍ የማስከፈልና  መንገድ ላይ ተሳፋሪዎችን የማጉላላት ችግሮች አልፎ አልፎ እየተስተዋሉ ይገኛል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ  ትራንስፖርትና መንገድ  ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አድማሱ ማሴቦ በበኩላቸው፤ ከትራፊክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘም ህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት እንዲችል የሁለቱም መዋቅር ባለድርሻ አካላት በጋራ በመሆን የመገምገምና የመከታተል ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ህዝቡ እያነሳ ያለውንና በሌሎች አከባቢዎች አገልግሎት ላይ የዋለውን የብሪጅንግ ቴክኖሎጂ አገልግሎትን ለማስጀመር ከክልል በተሰጠው አቅጣጫ በቅርቡ ወደ ሥራ ለመግባት ለህብረተሰቡ፣ ለአሽከርካሪዎችና ለባለሀብቶች ግንዛቤ ወደ መፍጠር ሥራ መገባቱንም ኃላፊው ገልፀዋል።

ዘጋቢ: ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን