በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል  አመራሮችና ሰራተኞች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ

“የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄ አካል የሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምርምር ማዕከሉ አመራሮችና ሰራተኞች በቅጥር ግቢ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ከ4ሺ በላይ ችግኞችን በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ተረፈ በተቋሙ ከምርምር ስራ ጋር በማቀናጀት  በየአመቱ ከሀምሌ ወር ጀምሮ በርካታ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በጋራ እየተከሉ መሆኑን አስታውሰው በተለይም አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም በዘንድሮ ዓመት ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ መነሻ ያደረገ ለምግብነት የሚውሉ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞችን እየተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢውን አግሮ ኢኮሎጂን መሰረት በማድረግ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን በመለየት ሲተከሉ መቆየቱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ በተለይም አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ የሙዝ ችግኞችና ሌሎችንም ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ተቋማትን የፍራፍሬ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር  ተወካይ አቶ ቢላል ተማም በበኩላቸው ተቋሙ አቅዶ ከሚሰራቸው ዝርያን የማሻሸልና የምርምር ስራዎች ባሻገር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በሌላ በኩል እንደ ክልል በሌማት ትሩፋት የተያዘውን ዕቅድ በማሳካት በእንስሳት ዘርፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ  በሰው ሰራሽና በመደበኛ የማዳቀል ዘዴ የላሞችን ዝርያ የማሻሸል ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉት የምርምር ማዕከሉ ሰራተኞች በሰጡት አስተያየት በማዕከሉና በተለያዩ አካባቢዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል እንደ ሀገር በአረንጎዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የድርሻቸውን  እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ናስር ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን