የመጤ ወራሪ ዝርያዎች መከላከልና ማስወገድ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ተካሄደ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደን አከባቢ፣ ጥበቃ ልማት ቢሮ የመጤ ወራሪ ዝርያዎች መከላከልና የማስወገድ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ለማ፤ መጤ አረሞች የአካባቢን ስነ ምህዳር በማዛባትና ጠቃሚ እጽዋቶችን በማጥፋት የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ፥ የተፈጥሮ ሚዛንን ጠብቆ ለማቆየት ለፍጡራን ህልዉና ወሳኝ መሆናቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የጎላ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

አካባቢን ሊበክሉ የሚችሉ ነገሮችን ወደ ሀብት ቀይሮ ለመጠቀም ሁሉም ዜጋ ድርሻ ያለዉ ቢሆንም የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች ኃላፊነት ጉልህ መሆኑን አቶ ንጉሱ ጠቁመዋል።

አቶ አብርሃም መጫ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው፤ የብዝሀ ህይወት ሀብት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አከባቢያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ከመሆኑም በላይ፥ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አይነተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን አመላክተዋል።

በሥነ-ምህዳር ውስጥ የሁሉንም አካላት ተፈጥሯዊ ሥርዓት ጠብቆ ማቆየት የህልዉና ጉዳይ በመሆኑ፤ ሁሉም የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣትና ለመፈጸም የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ስልቶችን ነድፎ  ሊሰራ እንደሚገባ አቶ አብርሃም ጠቁመዋል።

አረሞች የአካባቢውን ስነ ምህዳርና ጠቃሚ የሚባሉ እጸዋቶችን ከማጥፋት ባሻገር በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ናቸው ያሉት በመድረኩ የስልጠና ሰነድ ያቀረቡት አቶ አብርሃም አለማየሁ ናቸው።

በመድረኩ የተገኙት የዞንና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በቀረበው ሰነድና የመወያያ ሀሳብ ላይ በዝርዝር የመከሩ ሲሆን፤ የመጤ ወራሪ አረምን የመከላከልና የመቆጣጠሩ ተግባር በልዩ ትኩረት ሊመራ እንደሚገባው ተናግረዋል።

መጤ ወራሪ የእጽዋት ዝርያዎች ከተፈጥሮ መገኛ አልፈዉ በማንኛውም ሥርዓተ ምህዳር መላመድና መሰራጨት የሚችሉ ዕጽዋት፣ እንስሳትና ደቂቅ አካላት በመሆናቸው የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባሩ የአንድ ተቋም ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደማይገባው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ