በዓለም ዙሪያ ያለው የሙስሊም ማህበረሰብ የቅዱሱን ረመዳን ወር መገባደድ ተከትሎ የኢድ አልፈጥርን በዓል ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና ዘመድ አዝማድ ጋር በታላቅ ደስታ ያከብራል፡፡
በጎ አድራጎት፣ ከአላህ ጋር አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር እና ርህራሄን ማሳየት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በዚህ ወቅት የሚስተዋል ነው፡፡
በተለያዩ ዓለማት ታዲያ ኢድ አልፈጥርን የማክበር ልዩ ልዩ ልማዶች አሉ፡፡ ጥቂቶችን እንመልከት፡፡
ቱርክ፡-
በቱርክ ሀገር ኢድ አልፈጥር “ራማዛን ባያርሚ” ወይም “ስከር ባያርሚ” በመባል ይታወቃል፡፡ “ባያርሚ” የሚለው ቃል ክብረበዓል በሚል ይተረጎማል፡፡
በቱርክ የኢድ በዓል ለ3 ተከታታይ ቀናት ይከበራል፡፡ ቀናቶቹም ብሔራዊ የበዓል ቀናት ናቸው፡፡
በኢድ ወቅት በቱርክ በእድሜ አንጋፋ የሆኑ ሰዎችን ቀኝ እጅ መሳም በእጅጉ የተለመደ ነው፡፡ ወጣት ልጆችም ሻማ እና ባህላዊ ጣፋጭ ነገሮችን በስጦታ መልክ ይለዋወጣሉ፡፡ ከሚለዋወጧቸው ጣፋጭ ነገሮች መካከል ባቅላባ ይገኝበታል፡፡
የቱርክ አባቶች፣ እናቶች፣ ሽማግሌዎችና አዛውንቶች ደግሞ በዓመቱ ጥሩ ምግባር በማሳየት ምስጉን ሆኖ ለተገኙ ህጻናት የቱርክ ገንዘብ ሊሬ ይሰጣሉ፡፡
ኢንዶኔዥያ፡-
ኢድ አልፈጥር በኢንዶኔዥያ ሀገር “ሌብራን” በመባል ይታወቃል፡፡ በአብዛኛው ይህ በዓል በሚከበርበት ወቅት ከሀገሩ ወጥቶ የቆየ ሰው ወደ ቤት የሚመለስበት “ሙዲክ” የተሰኘ ልማድ አላቸው፡፡
በሙዲክ ልማድ መሠረት ከቤት እርቆ የቆየ ሰው በኢድ አልፈጥር ይመለስና ከቤተሰብና ወዳጀቹ ጋር በደስታ ያከብራል፡፡
ሌላኛውና በኢንዶኔዥያ በእጅጉ የሚታወቀው “የሀላል ቢሀላል” ልማድ ነው፡፡ በሀላል ቢሀላል ልማድ መሠረት ሁሉም የማህበረሰቡ አባል እርስ በርሱ ምህረት ማድረግና መቀበል ይኖርበታል፡፡
ባህላዊ ግዙፍ ኬክ መሥራት፣ ባህላዊ አልባሳትን መልበስ፣ ስጦታ መሰጣጠት፣ በእጅ የተጻፉ የመልካም ምኞት መግለጫዎች መለዋወጥ እና በሞት ያጡት ወዳጅ መቃብር ድረስ ሂዶ መጎብኘትና ፍቅር መግለጽ በኢንዶኔዥያ የኢድ ወቅት ልማዶች ናቸው፡፡
ማሌዥያ፡-
በማሌዥያ ኢድ አልፈጥር “ሀሪ ራያ ኤዲልፊትሪ” ይሰኛል፡፡ የእምነቱ ተከታዮችም ቤቶቻቸውን በባህላዊ ቀለም ያስውቡታል፡፡ እጅግ ለተወደዱ ወዳጆቻቸው በአካባው የሚታወቅ ባህላዊ ምግብ ያዘጋጃሉ፡፡ ከሩዝ የሚሠሩት በሀገሩ ቋንቋ “ኬቱፕታ” እና “ሬንዳንግ” በመባል የሚታወቁት የባህል ምግቦቻቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሁሉም ማሌዥያዊያን በኢድ ወቅት ለሁሉም ሰው በሮቻቸውን ክፍት የማድረግ ልማድም አላቸው፡፡ በሮቻቸውን ክፍት የሚያደርጉት ለተቸገሩ፣ ላልተቸገሩ፣ ለየትኛውም እምነት ተከታይ እና በየትኛውም መደብና የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሁሉ ነው፡፡
በርግጥ አብዛኛው የሙሲሊም ማህበረሰብ ኢድ አልፈጥርን በዓል እምነቱ በሚፈቅደው ልክ በተቀራረብ መልኩ ያከብራል፡፡ ይሁንና በምሥራቅ እና ምእራቡ ዓለም ያለው ባህላዊ የበዓል አከባበር ልማድ ከሀገር ሀገር ልዩ ልዩ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
አዘጋጅ፡ ማሬ ቃጦ
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ