“የተገኙ አማራጮችን እንደ እድል እጠቀማለሁ” ጋዜጠኛ ማርታ ደጀኔ

የንጋት እንግዳችን ጋዜጠኛ ማርታ ደጀኔ ትባላለች፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች በጋዜጠኝነት እና በጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ከ16 ዓመታት በላይ አገልግላለች፡፡ ዛሬም የእውን በጎ አድራጎት ማህበር መስራች፣ ስራ አስኪያጅ እና የመገናኛ ብዙሀን ሴት ጋዜጠኞች ማህበር የቦርድ አባል ናት፡፡ ከእንግዳችን ጋር በአካል ጉዳተኝነት፣ ሴትነት፣ ጋዜጠኝነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በገነት ደጉ

ንጋት፡- በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆንሽ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ማርታ፡- እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ትውልድ እና እድገትዎን ቢያስተዋውቁን?

ማርታ፡- ጋዜጠኛ ማርታ ደጀኔ እባላለሁ፡፡ ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ልዩ ስሙ አራት ኪሎ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን አፄ ናውድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ተከታትያለሁ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ከ9ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በመከታተል በ1996 ዓ.ም ጥሩ ውጤት አምጥቼ በ1997 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ካምፓስን ተቀላቀልኩ፡፡ በካምፓስም ቆይታዬ ትምህርቴን በጥሩ ሁኔታ በመከታተል በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ-ጽሑፍ የትምህርት ክፍል በመጀመሪያ ድግሪ ተመረኩኝ፡፡

አካል ጉዳት የደረሰብኝ በልጅነት ዕድሜዬ ከሁለት ዓመት በኋላ እንደሆነ ወላጆቼ ነው የነገሩኝ፡፡ ምክንያቱን ደግሞ የፖሊዮ ክትባትን በአግባቡ ተከታትሎ አለመውሰድ ያመጣው ችግር ነው፡፡ ወላጅ እናቴ እና አባቴ በግንዛቤ እጥረት ክትባቱ አንድ ጊዜ ይበቃል ብለው ችላ በማለታቸው ለአካል ጉዳት ችግር  ልጋለጥ ቻልኩ። 

ንጋት፡- አካል ጉዳተኛ መሆን ያስከተለው ተጽዕኖ እንዴት ትገልጪያለሽ?

ጋዜጠኛ ማርታ፡- አካለዊ ዕድገቱ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ  እንደሚመጣ ሁሉ አካል ጉዳተኝነቱ መገለልን ይዞ ይመጣል፡፡ አካል ጉዳተኛ ከብዙ ነገር የሚገድብ  በመሆኑ ምክንያት እንደማናቸውም አብሮ አደጎቼና  ጓደኞቼ አባሮሽ እሮጦ አለመጫወትና ሰኞ ማክሰኞ የምትያቸው ድብብቆሽ እንደ ልጅ በልጅነት ዕድሜዬ መቦረቁም ቀርቶብኛል፡፡ ይህም መገደብ ለማነባቸው ነገሮች እና ለማዳምጣቸው ነገሮች ይበልጥ እንዳደላ አድርጎኛል፡፡ 

በልጅነት ዕድሜዬ ቶሎ ትምህርት ቤት አልገባሁም፡፡ ትምህርት ቤት ቶሎ እንዳልገባ ያደረገኝ አካል ጉዳተኛ መሆኔ አይደለም፡፡ አካል ጉዳተኛ መሆኔም ጊዜው ቢቆይም ከትምህርት ቤት እንዳልገባ አልከለከለኝም፡፡ ነገር ግን ቤተሰብ ቆመሽ እንድትሄጂ እና ከሌሎች ልጆች እኩል እንድትሆኚ የመፈለግ ሁኔታዎች ስለነበሩ  ይህንን ፍላጎቴን ተንተርሰው ቤተሰቦቼ በየህክምናውና በየፀበሉ ሲያመላልሱኝ ብዙውን ጊዜዬን  አቃጥሎብኛል፡፡   ይህም ትምህርቴንም በወቅቱ እንዳልጀምር እንቅፋት ሆኗል፡፡

ንጋት፡- ቤተሰብ በልጅነት እድሜሽ ለህክምናው የሰጠው ትኩረት እንዴት ትገልጪያለሽ?

ጋዜጠኛ ማርታ፡-  ቤተሰቦቼ በወቅቱ ባህላዊ  ይሁን ዘመናዊ ህክምና ሞክረዋል። እኔን ለማሳከም አልቦዘኑም፡፡ አለ የተባለበት የህክምናም ይሁን ባህላዊ ህክምና መገኛዎች እንዲሁም ፀበልን ጨምሮ ያልደረሱበት የለም። እኔን ከሰው እኩል ለማድረግ  አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ የቤተሰቦቼ ልፋት፦  እኔን ሰው ለማድረግ የተሯሯጡባቸው ጊዜያትን አይረሱኝም። የቤተሰቦቼ ጥረት ትምህርቱን ለመከታተል ሳይሆን መጀመሪያ ህክምናውን ማስቀደም ነበር፡፡ ሳይሳካላቸውም “ሰው” እንደምሆን ያምኑ ነበር፡፡ ቤተሰቦቼ ትምህርት ቤት ሳያስገቡኝ በመቆየታቸው በመብልም ይሁን ቤት በማደርጋቸው በማናቸውም ጉዳዮች ማመጽ ስጀምር ትምህርት ቤት ሊያስገቡኝ ተገደዱ፡፡

ከምንም በላይ ፈጣሪን የማመሰግነው ዓዕምሮዬ ለማንኛውም ነገር ብሩህ  መሆኑ ነው። እቤት ውስጥ ቁጭ ባልኩበት ወቅት ጥሩ እውቀት እንዲኖረኝ  አስጠኝ ተቀጠሮልኝ ነበር። ትምህርት ቤት ከመግባቴ በፊትም ጥሩ የሚባል ዕውቀት ነበረኝ፡፡ 

ወላጅ አባቴ ከጎረቤቶች ጋር በመተባበር የቄስ ትምህርት ቤት  በመክፈት አቡጊዳ፣ ሀ ሁ እና መልዕክተ ዮሐንስን በአንድ ሳምንት አጠናከኩኝ። ይበልጥ ታላላቆቼ እና  ታናሾቼ የተማሩበትን መጽሐፍና ደብተር ተከታትሎ የማንበብ እና የሰሯቸውን የቤት ስራዎች  የማየት ልምዱ ነበረኝ። 

ንጋት፡- በትምህርት ያለሽ ዝንባሌ እንዴት ይገለፃል?

ማርታ፡- በትምህርቴ ጥሩ ተማሪ ነኝ፡፡  አልፎ ተርፎ እህቶቼንና የወንድሞቼን የቤት ስራ መስራት የዘወትር ልምዴ ነው፡፡  በመኖሪያ ቤታችን ሳሎን ውስጥ ማንም ሰው ፈልጎ አያጣኝም፡፡  የእኔ መገኛ የመጽሐፍ መደርደሪያው አጠገብ ነው። በዚህም ምን ታነቢያለሽ ብትይኝ ምንም ነገር አልመርጥም። ልበወለድ፣ፖለቲካው፣ ባዮግራፊ፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን ጭምር አይቀረኝም።  በዚህም አባቴ ገዝቶ ያመጣውን መጽሐፍና ጋዜጣ  መጀመሪያ እኔ እንዳነብ በማለት ቅድሚያ ይሰጠኛል፡፡

ድሮ የአብዛኛዎቻችን ቤቶች ግድግዳች በጋዜጣ ይለጠፉ ነበር፡፡ በወቅቱ ያሉ ጋዜጦችን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ሰርቶ አደር፣ አዲስ ዘመን እና የሀራጅ ጋዜጦችን ጭምር የማንበብ ልምዱ ነበረኝ፡፡ በተጨማሪም ከሱቅ የሚገዙ ዕቃዎች የሚጠቀለሉት በጋዜጣ በመሆኑ፡- መጠቅለያ ሆኖ የመጣውን ጋዜጣ ስጥተው አነበው ነበር።  ይህንን ያየው አባቴ ለዕድሜዬ የሚመጥንም ይሁን የማይመጥነውን የማውቀው ታሪክ የለም። ግን ሁል ጊዜ መጽሐፍ ገዝቶ በማምጣት ያስደምመኝ ነበር፡፡ የሬድዮ አድማጭ ነበርኩ። ጋዜጣ ማንበብ እና ሬድዮ ማዳመጥ ገና ትምህርት ቤት ሳልገባ ነው የጀመርኩት፡፡ 

ንጋት፡- ወደ ሬድዮ አድማጭ እንዴት ተቀላቀልሽ?

ማርታ፡- በልጅነት ዕድሜዬ በማንበብ እና በማዳመጥ የገነባሁትን ስብዕና ያደገው ነገር ለጋዜጠኝነት ሙያው ልዩ ፍቅር እንዲኖረኝ አገዘኝ፡፡ ያኔ እንደዚህ የሬድዮ ጣቢያ ባልበዙበት ኢትዮጵያ ሬድዮ፣ ለገዳዲ እና ፋና ከኋላ የመጣ ሲሆን ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን የአድማጮች ተሳትፎ ጥያቄ የኢትዮጵያ ሬድዮ ላይ ሲጀመር ቋሚ ተሳታፊ በመሆን ጥያቄ በመመለስ ስፖርትም፣ ፖለቲካም ይሁን ጠቅላላ እውቀት ማንኛውም ጥያቄ መመለስ ጀመርኩኝ፡፡ በዚህም ማርታ ደጀኔ ከአራት ኪሎ የሚለው ተለይቶ መታወቅ ጀመረ፡፡

በዚህም መንገድ የጀመረው ተሳትፎ እስከ ስምንት ዓመታት ድረስ ስሜ ከሬድዮ እንዳልጠፋ አድርጎኛል፡፡  ለገዳዲ፣ የኢትዮጵያ ሬድዮ ብሄራዊ አገልግሎት እና ፋና ላይ በጣም እሳተፍ ነበር። ከዚያም ታሜሶን ማታ ማታ የሚያዘጋጀው የቴሌቪዥን ጥያቄና መልስ ውድድር መጣ። እዛም ላይ በተመሳሳይ ብቅ አልኩኝ፡፡ ይህም ማርታ ደጀኔ ማናት? የሚለውን ጥያቄ ፈታ። ከአድማጭ ተመልካች ጋር አስተዋወቀኝ፡፡ ብዙው ሰው የቴሌቪዥን ጥያቄና መልስ ውድድር እስኪጀምር ድረስ አካል ጉዳተኛ እንደሆንኩኝ አያውቁም ነበር።  ብዙዎች በቢዝነሱ ዓለም በጣም የተሳካላት ዓይነት ሰው አድርገው ይስሉ ነበር፣ ስፖርተኛ አቋም ያላትም ሰው ያደርጉኝ ነበር፣ሌሎቹ ደግሞ ማንበብ ብቻ ስራዋ የሆነች ሴት አድርገው ይመለከቱኝም ነበር፡፡

ንጋት፡- እንዴት አድናቆትን አተረፍሽ?

ማርታ፡- ሲያበረታቱ እና ሲደግፉኝ የነበሩ ሰዎች ሰው ሆኜ ስገኝ ደግሞ አድናቆታቸውን መለገስ ጀመሩ፡፡

ንጋት፡- እንዴት ነበር  የጋዜጣ ዝግጅትና ህትመት የጀመርሽው?

ማርታ፡- የጋዜጣ ዝግጅት ሥራ የጀመርኩት የ12ኛ ክፍል ውጤት እስኪመጣ ሁለት ወር ከምቀመጥ ብዬ ነበር፡፡  ከዚያም የጋዜጣ ህትመት ፈቃድ ለማውጣት ጥረት አደረግኩ። በወቅቱ የግል ጋዜጣ በጣም ተነባቢ ነበር። የገንዘቡ አቅም ግን አልነበረኝም፡፡ ፈቃዱን ለማውጣት የሚያስፈልጉትን አስፈላጊ ነገሮችን ማሟላቴን አላውቅም ነበር፡፡ ግን ቀጥታ ፈቃድ ሰጪው መስሪያ ቤት በድፍረት ሄድኩኝ፡፡ ማሟላት ያለብኝን ገንዘብ እና ቁሳቁሶችን ነገረኝ። በተለይም ቢሮሽ ውስጥ ኮሚፒውተር እና በባንክ አካውንት የሚጠይቀውን የገንዘብ መጠን ነገረኝ። ገንዘቡን ከማክሮ ፋይናንስ እና ከዘመድ አዝማድ ተበደርኩ። የሚያስፈልገኝ  ገንዘብ 10ሺ ብር ነበር። በወቅቱ 10ሺ ብር ብዙ ብር ነበር፡፡

እኔ ግን የተገኙ አማራጮችን ሁሉ እንደ ዕድል እጠቀማለሁ፡፡ አካል ጉዳተኝነቴ ሌላ ዓለም እንዲያሳየኝ መንገድ አድርገዋለሁ፡፡ እኔ አካል ጉዳተኛ ነኝ ብዬ ማማረር፣ ጨለምተኝነት፣ ማርጎምጎም ብዙ ቦታ የላቸውም፤ ከሚባለው በላይ መንፈሰ ጠንካራ ነኝ፡፡

ኮምፒውተሩን እንዴት ላግኝ? እያልኩ ሳስብ ታሜሶን ያኔ ሀሙስ ማታ ባለው የቲሌቪዥን ፕሮግራም ጥያቄና መልስ ውድድር ይሸልም ነበር። እርሱን ለምን እንደ አማራጭ አልጠቀምም በማለት ወደ ዝግጅት ክፍሉ  ሄድኩኝ፡፡ በወቅቱ ያለውን ታሜሶን ማናጃር አናገርኩ፡፡ ሳናግረው ለዚህ ማሟያ ነው አላልኩም ነበር፡፡ በወቅቱ መወዳደር እፈልጋለሁ ብቻ ነበር ያልኩት፡፡ ምንም ችግር እንደሌለው አበረታታኝ፡፡ ገብቼም ተመዘገብኩኝ፡፡ በብቃት በጥሩ ውጤት አሸንፌ ኮምፒውተር ተሸለምኩ፡፡

በወቅቱም ዋናው ዓላማዬ ኮምፒውተሩን አግኝቼ ፍቃዴን መውሰድ ነበር፡፡ ግን አቋራጩ መንገድ ዕድል ይዞ መጣ፡፡ ፈጣሪንም አመሰገንኩ። ኮምፒውተሬን ይዤ ቢሮዬን አሟልቼ ፍቃድ ሰጪው አካል ጎበኘውና የጋዜጣ ህትመት ፈቃድ በ1996 ዓ.ም ገና ዩኒቨርሲቲም ሳልገባ ነበር የተሰጠኝ፡፡

ንጋት፡- ጋዜጣው በየስንት ጊዜ ይታተም ነበር ስንትስ ገጽ ነው? ይዘቱስ?

ማርታ፡- ጋዜጣው ሳምንታዊ እና ባለ ስምንት ገጽ ነበር፡፡ የጋዜጣው ይዘት አካል ጉዳተኝነት፣ ማህበራዊ ጉዳይ እና የወጣቶችን  ህይወት የሚዳስስ ጋዜጣ ነው፡፡  የጋዜጣው ስያሜ “እውን”ይባላል፡፡

ከዚያም የማውቃቸው ጓደኞቼን፣ በሬድዮ ላይ ይሳተፉ የነበሩ፣ ስምንት ወጣቶችን በማሰባሰብ አንዳንድ ዓምድ እንዲይዙ በማድረግ ይጽፉ ነበር። እኔ ግን ታይፕ በማድረግና በማዘጋጀት ማተሚያ ቤት ወስጄ አሳትም ነበር፡፡

በዚያን ወቅት የሙያው ፍቅር እና ፍላጎት እንጂ እውነት ለመናገር ስለ ገንዘብ አስቤም አላውቅም። በዚያን ወቅት ማስታወቂያ የሚያስነግሩትንና እስፖንሰር ማፈላለግ ይቻል ነበር፡፡ ከማይክሮ ፋይናንስ የተበደርኩት ብር እስኪያልቅ ድረስ የህትመት ስራው ቀጠለ፡፡

በሳምንት 1ሺ ኮፒ ቦሌ ማተሚያ ቤት ይታተም ነበር፡፡ ጋዜጣው በወቅቱ 1ብር ከ50 ሳንቲም ነው የሚሸጠው፡፡ እውነት ለመናግር ሶስት መቶ ጋዜጣ አይሸጥም ነበር፡፡ በዓመቱ ምርጫ 97 መጣና ግርግር ተፈጠረ፡፡ በወቅቱም እነ ሳተናው፣ ወንጭፍ የሚባሉ ጋዜጦች ነበሩ፡፡ በዚህም የእኔ ጋዜጣ እነዚህን ጋዜጦች ተቋቁሞ መውጣት አልቻለም ነበር፡፡

ንጋት፡- ለምንድነው ተወዳዳሪ መሆን ያልቻልሽው?

ማርታ፡- “እኔ ብዙ ጊዜ ፖለቲካ አልደፍርም፤ ፍላጎቱም የለኝም”፡፡ ጓደኞቼ ግን ገፋፍተውኝ ነበር፡፡ በማላውቅበት አልገባም ብዬ ብድሩን ከፍዬ ወደ 11ኛ ህትመት ላይ እያለ ጋዜጣው ቆመ። ልክ እሱ ሲቆም ውጤት መጣ፡፡

ንጋት፡- በወቅቱ ውጤት እንዴት ነበር?

ማርታ፡- ፈጣሪ ይመስገን ጥሩ ውጤት ነው ያመጣሁት፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት የትምህርት ክፍልን ተቀላቀልኩ፡፡ የእኔ ህልም የነበረው 1ኛ የእረፍት ጊዜዬን በከንቱ ማባከንን አልፈለኩ፡፡ ሲቀጥል የጋዜጠኝነትን ህልም እውን ለማድረግ ስለፈለኩኝ ነበር፡፡ ጋዜጣዋንም ለዚህ ነው ስያሜዋ እውን ያልኩት፡፡ ወደቅሽም ተነሳሽም አጋጣሚዎችን መሞከሩ ጥሩ ነው። እኔ በመሞከር አምናለሁ፡፡ ስለሞከርኩም ነው ያወቅኩት። የጋዜጠኝነት ህልሜን አሳክቻለሁ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ሲቀጥል ስትሞክሪ ነው ፈጣሪም የሚረዳው፡፡ ያንን ጊዜ እንደ ድል ቆጥሬዋለሁ፡፡

ንጋት፡- ከዩኒቨርሲቲ ቆይታሽ በኋላስ?

ማርታ፡- ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ላይ እያለሁ የግል ኤፌ.ኤሞች ወደ ዩኒቨርሲቲው መምጣት ጀመሩ፡፡ በዚህም ዩኒቨርሲቲ ገባሁ ብዬ አልቦዘንኩም፡፡ ዛሚ 90.7 ጣቢያ ላይ አመለከትኩ። እዛው ላይ ሲቪዬን ላኩኝና ተጠራሁ፡፡ የሚሚ ስብሀቱ ጣቢያ ነበር፡፡ ፈተና ተፈትኜ በማለፍ ስልጠና ተሰጥቶኝ ከብዙ ጋዜጠኞች መካከል በአቀራረብም በድምጽም ጥሩ ውጤት በማምጣት ሁለተኛ ወጥቼ መደበኛ ጋዜጠኝነቱ ተቀላቀልኩ፡፡

ንጋት፡- አካል ጉዳተኝነት እና ጋዜጠኝነት እንዴት አገኘሽው?

ማርታ፡- የማሰራጪያ ጣቢያው ቢሮው ሶስተኛ ፎቅ ላይ ነው፡፡ በወቅቱ አለቃዬ ሴት ስለነበረች ሳናግራት መስራት እንደምችል እና አካል ጉዳተኝነቴ ከሥራው እንደማያግደኝ ነገረችኝ፡፡ ከምንም እርሷም ጥሩ ብርታት ሆነችኝ፡፡ የእኔም ጥንካሬ ሲጨመርበት ይበልጥ አጠነከረኝ፡፡

ምክንያቱም አትችይም የሚል ነገር አልነበራትም፡፡ እንደ መደበኛ ሪፖርተር ወጥቼ ዜና በጊዜ ዘግቤ ነው የምወርደው፡፡ ይህም ነፃነቱ ደስ አለኝ፡፡ በዚህም እዛው ጥሩ ጥሩ ሥራዎችን ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በስፋት እንዲሰራ ከኃላፊዬ ጋር መስራት ጀመርን። እኔ ስላለሁ በአንድም በሌላ መልኩም የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ እንዲነሳ ትልቅ በር ከፈተ፡፡

በቀጥታ ፕሮግራም እንግዶችን እየጋበዝኩ ብዙ ስራዎችን ሰራን፡፡ አንድ አራት ዓመት እንደሰራሁ በ2001 ዓ.ም ወደ ትዳር ዓለም ተቀላቀልኩ፡፡

ንጋት፡- አካል ጉዳተኝነት እና እናትነትን እንዴት አገኘሽው?

ማርታ፡- አካል ጉዳተኛነት እና እናትነት ከባድ ነው፡፡ በፊት ምንም ነገር የማያሳስበኝ ነፍሰ ጡር ስሆን ማሰብ ጀመርኩ፡፡ መፍራት እና መስጋት ጀመርኩ፡፡ በጣቢያው አምስት ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ አመለከትኩና ስራዬን አቆምኩ፡፡ በ2002 ዓ.ም የመጀመሪያ ልጄን ወለድኩ፡፡

ባሳለፍኳቸው ጊዜያት ሁሉ ሞገስ እና ፀጋ የሆነኝ እግዚአብሔር ነው፡፡ ፈጣሪ ደግሞ ይደግፋል፡፡ በጎዶሎሽ ውስጥ እግዚአብሔር ሙሉ ነው፡፡ “እግዚአብሔር ላይጠግን አይሰብር”፣ የሚባለው አባባል ለእኔ ነበር አልኩ፡፡

በዓመቱ ደግሞ ሁለተኛ ልጄን ደገምኩ። ሁለቱንም ልጆች እያሳደኩ ብዙ የጋዜጠኝነት እንቅስቃሴ አልነበረኝም፡፡ ልጆቼን ማሳዳግ ላይ ትኩረት አደረኩ፡፡ ቤተሰቦቼ ያግዙኛል ነገር ግን ልጆቼ አጠገብ በመሆን ማሳደግን ፈለኩ፡፡

ልጆቼም ከፍ ሲሉ በ2005 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሮድ ካስት ኮርፕሬሽን ከኢቲቪ ጋር የአየር ሰዓት በትብብር ወስጄ ”ማእዶት” የሚባል በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰራ ፕሮግራም ቀርጬ ኢቲቪ 3 ይባል የነበረው ላይ መዝናኛ ፕሮግራም መስራት ጀመርኩ፡፡

ማእዶት ማለት መሸጋገሪያ ማለት ነው። አካል ጉዳተኞችን ከመንግስት ጋር፣ ከህብረተሰቡ ጋር ለማገናኘት እንደ ድልድይ ይሆናል ብዬ ነው ስያሜውን የሰጠሁት፡፡ እውነት ለመናገር በጣም ጥሩ ፕሮግራም ነበር፡፡

በተመልካቹም ዘንድ በጣም ተወዳጅ ነው። በዋናነት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ እና ፍለጋ የሚል ዝግጅት ነበረው፡፡ ይህም አካል ጉዳተኞችን ፈልገን የተሳካላቸውም ያልተሳካላቸውንም ህልማቸውን፣ ሀሳባቸውን፣ ችግሮቻቸውን እና ምኞታቸውን የሚገልፁበት ፕሮግራም ነበር፡፡

አካል ጉዳተኞች እኛ ጋር መምጣት ሳይሆን እኛ አካል ጉደተኞችን ፈልገን ወደ አድማጭ ተመልካቹ ጋር የምናደርስበት ሲሆን ሌላው  ዝግጅት ደግሞ “የመረጃ ቋት” ይባላል፡፡ እርሱ ደግሞ አካል ጉዳተኝነት ከመከሰቱ በፊት እንዴት እንጠንቀቅ፣ አካል ጉዳተኝነት ከተከሰተ በኋላ ምን እናድርግ የሚሉ መረጃዎችን የሚሰጥ ነበር፡፡ 

አካል ጉዳተኞች በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ላይ በዘመናዊ ውዝዋዜ፣ ዳንስ፣ በሰርከስ፣ በግጥም፣ በስነ-ጽሑፍ ሁሉም አካል ጉዳተኞች ያካተተና አዝናኝ ነበር፡፡ ፕሮግራሙ ሳምንታዊ ቢሆንም ይደገማል፡፡ ትልቁ ነገር “ማእዶት“ በማናቸውም የዓላት ቀናትም ያዘጋጅ ነበር፡፡ በዚህም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን፣ ወጣቶችን፣አንጋፋዎችን ሰብስበን አካል ጉዳተኞችን ብቻ ሳይሆን አዝናኝ እና የበዓል ይዘት ያላቸው፣ግን ደግሞ ዓላማችንን ሳንረሳ አካል ጉዳተኞችን በማምጣት እንዲዘፍኑ እና መድረክ መሪ እኔ በመሆን ለ1 ሰዓት ከ30 ደቂቃ እናስተምር ነበር፡፡ በዚህም አጋሮችን አገኘን፡፡ ኢቢሲ ይዘቱን ሲያሻሽል በተለይም ጠንከር ባሉ ጉዳዮች ላይ ፈታኙ ብዙ ነውና ይዘቱን ሲቀይር በ2011 ዓ.ም ፕሮግራሙን አቆምኩ፡፡

ሶስተኛ ልጄንም ወለድኩ፡፡ እንግዲህ የሶስት ልጆች እናት ሆንኩ፡፡ ባለቤቴም በዚህ ስራ በጣም ያግዘኛል፡፡ ትልቁ አጋሬም እርሱ ነው፡፡ ጉዳይ የማስፈፀም የማስታወቂያ እና የመሯሯጥ ስራዎችን የሚሰራው እርሱ ነበር፡፡ ጋዜጤኛ አይደለም፤ ግን በጋራ ነው የምንሰራው፡፡

ንጋት፡-  ያኔ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው እሳቤ እና ተግዳሮቶችንስ እንዴት ይገለፃል?

ማርታ፡- በማህበረሰባችን ውስጥ አካል ጉዳተኞች  ላይ አሁንም ያለው አመለካከት በተለይ ሴቶች ላይ ፈጣሪ የሰጠሸ የእናትነት የተፈጥሮ ፀጋ እንደሚገባሽ አይታመንም፡፡ ለምሳሌ ልጅ ወልዶ ማሳደግ፣ የትዳር አጋር መሆን እና የፍቅር ተጋሪ መሆን ለአካል ጉዳተኞች የተገደበ ወይም የተከለከለ ተደርጎ ነው የሚታሰበው፡፡ እኔም በዚህ ሂደት ብዙ ነገሮች ገጥመውኛል፡፡ እኔ ግን በማንበብ የገነባሁት ስብዕና  ፈጣሪ በረዳኝ ልክ ውስጤን ስለገነባሁ ችግሩ ብዙ ወደ ውስጤ አይገባም፡፡

በእርግዝና ወቅት አካል ጉዳተኛ ሆኖ ክራንች ይዞ ነፍሰጡር መሆን ለብዙዎች ድንግጥ የሚያደርግ ነገር አለው፡፡ ክትትል የማደርግበት የጤና ተቋም ደረጃው አይመችም ነበር፡፡ አሁን እየሰራሁ ያለው ስራ የእኔ ህይወት ተሞክሮ ወደ እዛ አንድንደረደር አድርጎኛል፡፡

2011 ዓ.ም ልክ ማእዶት እንደቆመ የማህበሩ ዓላማ በሴት አካል ጉዳተኞች ጤናና ስነ- ተዋልዶ ግንዛቤ ላይ ይሰራል፡፡ አካል ጉዳተኛ ሴቶች የመውለድ ፀጋ መነፈግ የለባቸውም፡፡ ይህንን ለመስራት የተነሳሳሁት በህይወቴ ከገጠመኝ ከራሴ ህይወት ተሞክሮ ነው፡፡

በጤና እና ስነ- ተዋልዶ አንዲት እናት የጤና ተቋሙ ሊመቻት ይገባል የሚል ጽኑ እምነት ነበረኝ፡፡ የጤና ባለሙያውም ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ ድርጅቱም ይህንን ስራ ነው የሚሰራው። በዚህም ድርጅት ግንዛቤ እና ስልጠና መስጠት፣ ተቋማትን ተደራሽ ማድረግ፣  ለባለድርሻዎች ሀሳብ የማስረጽ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

ይህንንም በጎ አድራጎት ድርጅት ከባለቤቴ ጋር ሀሳብ አመንጭተን ነው የጀመርነው፡፡ ከዚያም ፍቃድ ለማውጣት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተን ህጋዊ እውቅና አግኝተን ስራችንን እየሰራን ነው፡፡

ዋናው ዓላማ ሴት አካል ጉዳተኞች በሰነ- ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የገጠማቸውን ችግሮች እና ተግዳሮትን እንዲያቃለሉ ማድረግ ነው፡፡

ሁለተኛው ዓላማ ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ለምሳሌ ክራንች፣ዊልቸር ለአካል ጉዳተኞች መሰረታዊ ቁስ ነው፡፡ ከዚህም ውጪ ልታደርጊው አትችይም፡፡ ነገ የልማት ሀይል ስታስቢ እነዚህ ነገሮች መሟላት አለባቸው፡፡

እኛ ሀገር ላይ ስትመጪ ደግሞ ለአካል ጉዳተኞች ብዙ ነገሮች የተመቻቹ አይደሉም፡፡  አብዛኛው ነገር ከውጪ ሀገር ነው የሚመጣው። የብዙዎች አካል ጉዳተኞች የኢኮኖሚ ሁኔታ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ነገሮችን በደንብ እንቃኛቸው ነበር፡፡

ለምሳሌ በአዲስ አበባ ላይ ለ35 እና ለ40 ዓመታት ከቤት ያልወጡ ፀሐይን ማየት ያልቻሉ አካል ጉዳተኞች ገጥመውኛል፡፡ ምንድነው ብለሽ ቀርበሽ ስትጠይቂ የአካል ድጋፍ አላገኘንም ነው የሚሉት፡፡

ዊልቸርና ክራንች ቢኖር መስራትና መማር የሚችሉ ነበሩ፡፡ ያ ግን አልሆነም፡፡ እና ለምን ከውጪ ብቻ ጠባቂ እንሆናለን? ሀገር ውስጥ ባሉ ቁሳቁሶች ዊልቸሩን መገጣጠም አንችልም ብለን ወርክ ሾፕ ጀመርን፡፡ በዚያም ወርክ ሾፕ ዊልቸሮችን መገጣጠም ቻልን፡፡

ንጋት፡- ምን ያህል ውጤታማ እና ተደራሽ ናችሁ?

ማርታ፡– በጣም አቅም ለሌላቸው በነፃ በመስጠት ወደ ትምህርት ቤት እንዲቀላቀሉ ማድረግ እና ወደ ሚፈልጉት ስራ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ችለናል፡፡ ተቋሙ ዘንድሮ አምስተኛ ዓመቱ ነው፡፡

በዓላማና በሀሳብ ደረጃ ውጤታማ ነው። ግን የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ስራ በአንድ ጊዜ ብድግ የሚል አይደለም፡፡ ነገ ግን የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ እኔ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ የዚህም መስራች እና ዋና ሥራአስኪያጅ በመሆን አሁን ሥራ ላይ ነኝ፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያ ሴቶች ማህበር የቦርድ አባል በመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት እያገለገልኩ ነው፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባል በመሆኔ የሴት አካል ጉዳተኞች ጋዜጠኞች  ድምጽ በመሆን የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ሀሳቡ፣ ሙያው እና እውቀቱ ላላቸው አካል ጉዳተኞች ወደ ሙያው እንዲቀላቀሉ ተነሳሽነትን እፈጥራለሁ፤ አመላክታለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

ሲቀጥል ስለ አካል ጉዳተኞች እንዴት እንዘግብ፣ እንፃፍ፣ ምን ይባላል በሚለው ረገድ ደግሞ ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት እኔ እንደ ማሳያ በመሆን ከራሴ ተሞክሮ እና ከሰራኋቸው ስራዎች በተጨማሪ ግብዓት የሚሆኑ ነገሮችን በማመንጨት በተለያዩ የክልል ከተሞች ስልጠናዎችን በመስጠት የራሴን አስተዋጽኦ እያበረከትኩ ነው፡፡

ንጋት፡- የምታስተላልፊው መልዕክት ካለሽ?

ማርታ፡- ልጆቼን አሳድጋለሁ ትዳሬንም እየመራሁ ነው፡፡ ችግሮች የሉም እያልኩ አይደለም፡፡ ፈጣሪ ከፊትሽ ከቀደመ የሚያደናቅፍሽ ነገር አይኖርም፡፡  በእግዚያብሔር ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ በእርሱ እደገፋለሁ፡፡

ጋዜጠኛ ሳልሆን አንድ ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግልኝ ምን መሆን ትፈልጊያለሽ ሲለኝ ጋዜጠኛ መሆን ነበር ያልኩት፡፡ ያልኩት በቀልድ ሳይሆን እውነቴን ነው ያልኩት፡፡

በጣም ነው የተገረመው፤ ጋዜጠኝነት ሩጫ የሚጠይቅ ሙያ ነው፡፡ አንቺ ግን አካል ጉዳተኛ ነሽ እንዴት ነው ተሯሩጠሸ የምትሰሪው? ነው ያለኝ፡፡ ስለዚህ በእጅሽ ባለው  ጥበብ ላይ ብታተኩሪ በማለት ነው አቅጣጫ የሰጠኝ ይህም ለእኔ ተግዳሮት ነበር፡፡ 

የመጀመሪያ ልጄን ነፍሰጡር ሆኜ እንዴት አካል ጉዳተኛ ያረግዛል ያለኝም ነበር፡፡ ይህም ለእኔ እንቅፋት ነበር፡፡ ብዙ እንዲህ ነው ብዬ የማልጠቅሰው ነገር አለ፡፡ እኔ ተግዳሮቶችን ከፊት አስቀድሜያቸው አላውቅም፡፡ ከተግዳሮቱ በኋላ ያለውን ስኬት ነው የማስበው፡፡

ንጋት፡- በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

ማርታ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡