ሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ እውቀት ጋር በማዋሀድ ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ
ዩኒቨርሲቲው በስርአተ ትምህርት ክለሳ እና በሀገር በቀል እውቀቶች ልማት ትስስር ላይ የምክክር መድረክ አካሄዷል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል እንደገለጹት ሀገራችን ኢትዮጵያ የሀገር በቀል እውቀት ማማ የሚያሰኛት የበርካታ የሀገረሰብ እውቀት ባለቤት ናት።
ሀገር በቀል እውቀትን የሳይንስና የምርምር ውጤት ከሆነው ከዘመናዊ እውቀት ጋር ማዋሀድ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው ለሀገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ዶ/ር ፋሪስ የጉራጊኛ እና ሌሎች በቀጠናው ያሉ ቋንቋዎችን ለማልማት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የመማር ማስተማር ስራዎችን ለማከናወን የስርአተ ትምህርት ክለሳ እየተደረገ መሆኑና የስርአተ ትምህርት ክለሳው የሀገር በቀል ቅኝት እንዲኖረው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በዘመኑ የነበሩ ሀገረሰባዊ እውቀቶችን የዚህ ዘመን ትውልድ ጠቀሜታቸውን ተረድቶ መጠቀም እንደሚኖርበትና ይህም ዘመኑን በዋጀ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲሁም በቴክኖሎጂ በመደገፍ ነባር መሰረቱ ሳይለቅ ምርምርና ፍተሻ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሀንስ ገብሩ በዩኒቨርሲቲው በቋንቋ፣ በባህል እና በሀገር በቀል እውቀቶች በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑና ሀገር በቀል እውቀቶች ሰንዶ በስርዓተ-ትምህርት ለማካተት እየተሰራ ነው ብለው ጥቅም ላይ እንዲውሉና ለትውልዱ ለማስተላለፍ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዩኒቨርሲቲው የቋንቋ ባህል እና ሀገር በቀል እውቀቶች ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ካሚል ኑረዲን እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል ዕውቀትን ከሳይንሳዊ እውቀት ጋር በማስተሳሰር በመሰነድና ምርምር በማድረግ ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው እየተደረገ ይገኛል።
ሀገር በቀል እውቀቶች በስርአተ ትምህርት ለማካተት እየተሰራ እንደሚገኝና ለውጤታማነቱም ሁሉም አካላት ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ አብራርተዋል።
በመድረኩ ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋና ባህል በማሳደግና ሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ እውቀት ጋር በማስተሳሰር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በቀጣይም የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በተለይም የማህበረሰቡን ሀገር በቀል እውቀትን በትምህርት አካቶ በማስተማር ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ጨምረው ገልጸዋል።
በመድረኩ ከፌደራል፣ከዩኒቨርሲቲው፣ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ከጉራጌ፣ከምስራቅ ጉራጌ ዞኖችና ከቀቤና ልዩ ወረዳ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የወተት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በወላይታ ዞን የጉኑኖ ሀሙስ ከተማ አስተዳደር ገለጸ
የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በዓል የጋራ ትርክቶችን በማጉላት ልናከብር እንደሚገባ ተገለፀ
ብዝሀነትን በማስተናገድና ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን መከበር ፋይዳው የጎላ መሆኑን የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቴን ገለፁ