ሀዋሳ: የካቲት 07/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) 5ቱ የለውጥ አመታት በርካታ ድሎች የተመዘገቡበት መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ገለፁ::
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ “ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት ለዘላቂ ሠላምና ልማት” በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው::
የውይይት መድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ ለመሥራትና ለመምከር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየተካሄደ የሚገኝ መሆኑን በመድረኩ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ገልፀዋል፡፡
ከሰሞኑ በአማራ ክልል በ15 ከተሞች እና በኦሮሚያ ክልል በ20 ከተሞች የህዝብ ውይይት መድረክ መካሄዱንም አንስተዋል::
በዛሬው እለትም በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ከተሞች ተመሳሳይ የህዝብ ውይይት መድረክ እየተካሄደ ሲሆን የውይይት መድረኩ ዋና አላማም ከለውጥ ወዲህ በተመዘገቡ ስኬቶች ታቅደው ያልተሳኩና በለውጡ ሂደት ባጋጠሙ ፈተናዎች እና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ነው ብለዋል::
መንግስትና ህዝብ በሀገራዊ የእድገትና የለውጥ ጉዞ የራሱን ድርሻ የሚያበረክትበትን ሁኔታ መፍጠርም ከመድረኩ የሚጠበቅ ነው ብለዋል::
“ባለፉት አምስት የለውጥ አመታት በርካታ ድሎችን አስመዝግበናል:: አሁንም በፈተናዎች ውስጥ ሆነን ውጤት እያመጣን ነው::” ብለዋል ሚኒስትሯ::
የጋሞ ህዝብ ለሀገራዊ ለውጡ ያበረከተው ድርሻ ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ ናቸው::
ኃላፊው በአምስቱ የለውጥ አመታት የተመዘገቡ አበይት ድሎችን አብራርተዋል::
በማብራርያቸውም የመጀመሪያው ፖለቲካዊ ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል:: ዜጎችን ባይተዋርና ቤተኛ ያደርግ የነበረውን ሥርዓት መቀየር አስፈላጊ እና በህዝብ ዘንድ ታምኖበትና ትልቅ ትግል ተደርጎበት የመጣ መሆኑን ተናግረዋል::
ፖለቲካዊ ለውጡም በሀሳብ እንጂ በነፍጥ ሊሆን እንደማይገባ በማመን የተሰራበት ነው ብለዋል::
የቀድሞ የደቡብ ክልል ህዝብ ጥያቄ የተደመጠውና ምላሽም ያገኘው በለውጡ መንግስት ነው ያሉት አቶ ሳዳት በተለያዩ መስኮች በፖለቲካዊ ለውጥ እምርታዊ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል::
ኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት በእዳ ጫና ሥር የወደቀች እና የደቀቀ ኢኮኖሚ ውስጥ የነበረች መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ይህን ለመቀየርም የለውጥ መንግስት ኢኮኖሚውን ሪፎርም በማድረግ በርካታ ኢኮኖሚያዊ እድገቶችን አስመዝግቧል ብለዋል::
ግብርናውን ከማዘመን ጀምሮ ኢንዱትሪዎችና የቱሪዝም ዘርፍን የማነቃቃት ሥራዎች ተሰርተዋል::
አዳዲስ ፈጠራዎች፣ ሰፊ የስንዴ ልማት፣ ልማት፣ የሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ አረንጏዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ ገቢ ምርትን ማስቀረትና በምግብ እራስን ከመቻል አልፎ ወደ ውጭ መላክ ደረጃ ላይ የደረሰች ሀገር መሆኗንም አስረድተዋል::
ለውጡ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጉ ሀገር እንድትቀጥል እና ኢኮኖሚው እድገት እንዲያስመዘግብ አስችሏል::
በ2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ የሚጨበጥ ተስፋ ላይ እንድትደርስ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል::
በዲፕሎማሲው መስክም የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና የህዝቦቿን ክብር የሚያስጠብቁ ተግባራት መከናወናቸውን እና ውጤት ማምጣታቸውን አስታውቀዋል::
የባህር በር ለማግኘት በተደረገው ጥረት የተዘገበውን ስኬትም በአብነት ጠቅሰዋል::
“በርካታ ለውጥ ታይቷል:: አሁንም ግን ፈተናዎች አሉ” ያሉት አቶ ሳዳት ዛሬም ነፍጥ በማንገብ የሚያምን ፅንፈኛ ሀይል መኖሩን አንስተዋል::
ኑሮ ውድነትና ሌሎችም የወቅቱን ፈተናዎች መሻገር የሚቻለው በውይይት እና በአንድነት በመሆኑ ይህን ተገንዝበን ሁላችንም ለሀገራችን ስኬታማ የብልፅግና ጉዞ የድርሻችንን እንወጣ ብለዋል::
በአርባምንጭ ከተማ “ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት ለዘላቂ ሠላምና ልማት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው የውይይት መድረክ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው::
ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ