በሐይማኖት የመቻቻል ፎረም ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋት እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥር 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኮሬ ዞን አስተዳደር በሐይማኖት የመቻቻል ፎረም ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የኮሬ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የምስረታ ጉባኤውን አካሂዷል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ፥ የምክር ቤቱ ጉባኤ የዞኑ የህዝብ አደረጃጀት ጥያቄ በተመለሰበት እና የሙስሊም ወንድሞች ጥያቄ በመንግስት ይሁንታ አግኝቶ ምላሽ እየተሰጠ ባለበት ማግስት የሚደረግ ጉባኤ በመሆኑ የተለየ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዞኑ የተለያየ የተፈጥሮ ሀብት ያለው በመሆኑ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ነን ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ ለሁሉም ግን ሠላም መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
ሙስልም ወንድሞችና እህቶች ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር ተከባብረው እና ተቻችለው አደረጃጀቱን እየገነቡ መምጣታቸውን የገለጹት አቶ ታረቀኝ፥ በሐይማኖት መቻቻል ፎረም ውስጥ ያለንን መልካም ተሞክሮ ማስፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በሠላም እሴት ግንባታ ውስጥ እንደሀገር የተቀመጡ ግቦችን በጋራ የምናከናውንበትና የወጣቶችና የሴቶች የውሳኔ ሰጭነትን የምናጠናክርበት መሆኑን መዘንጋት የለበትም ብለዋል።
የሠላም እሴት ግንባታ ውስጥ፣ በሠላም ወጥቶ በሠላም ለመግባት፣ በአንድነት ለመኖር፣ አደረጃጀቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የኮሬ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ተወካይ አቶ ሰባኪ ሰለሞን፥ ሙስሊሞች በሰላም እሴት ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቁመው፥ የሚመሰረተው ምክር ቤትም ከዚህ የበለጠ ለመስራት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ እና የቀድሞ የኮሬ ዞን እስልምና ጉዳይ ዋና ፕሬዚዳንት ሸክ ዑመር ኡስማን በበኩላቸው፥ ከእያንዳንዱ ለውጥ ጀርባ የህዝበ ሙስልሙ ድርሻ አለበት ብለው፣ የለውጡ መንግስትም የነበሩ ጥያቄዎችን በመፍታት ህጋዊ ሰውነት እንዲኖር ማስቻሉ አስደሳች ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሀጂ ያሲን ከድር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕረዚዳንት እና የዕለቱ ክቡር እንግዳ እንደተናገሩት፣ በሪፎርሙ አሰራር መነሻ በክልሉ ባሉ ዞኖች የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት እየተመሠረተ መሆኑን ተናግረዋል።
የዚሁ አካል የሆነው በኮሬ ዞንም የተመሠረተ ሲሆን የሙስሊም ሴቶችና ወጣቶች ዘርፍ ምስረታም መካሄዱን ጠቁመዋል።
ሀጂ ያሲን በውይይት ተነጋግሮ በሰለጠነ መልክ ችግሮችን የሚፈታ ትውልድ እንዲኖር ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ