የወጣቶች የማስፈጸም አቅምን ማሻሻልና የስብዕና ማእከላት ግንባታን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወጣቶች የማስፈጸም አቅምን ማሻሻልና የስብዕና ማእከላት ግንባታን ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የየክልሉን ወጣትችና ስፓርት ቢሮ የግማሽ አመት አፈጻጸም ገምግሟል።

ቢሮው የ6 ወር አፈጻጸም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በቀረበው ሪፖርትና የመስክ ምልከታን መነሻ በማድረግ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን የወጣቶች ተጠቃሚነት አናሳ መሆንና ትኩረት የሚሹ ተጋላጭ ወጣቶች በምግብ ዋስትና ሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ቁጥር ማነስ ሊታረም የሚገባ መሆኑን ገምግመዋል።

የወጣቶች ስብእናና አመለካከትን ከማጎልበት ረገድ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባና በስፓርቱ ዘርፍ የተጠናከረ ስራ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢርሻሎ ኢርካሌ በሰጡት ምላሽ ተጋላጭ ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ያለውን ውስንነት በቀጣይ እናርማለን ብለዋል።

አቅመ ደካሞችን ከመርዳት ረገድ ያለው በጎ ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሰራለን ያሉት አቶ ኢርሻሎ የወጣቶች ስብእና ግንባታና መጤ ልማዶችን ከማረም አኳያ እንሰራለን ብለዋል።

የስፖርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ  አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ የሰው ሀይል አለመሟላትና የክልሉ በአዲስ መልክ መደራጀት ተግዳሮት የፈጠረ ነው ብለዋል።

በክልሉ ምክር ቤት ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እመቤት ወንድሙ ነባር ማህበራትንና ነባር ፌዴሬሽኖችን ከማጠናከር አንጻር ሰፊ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቅሰው የወጣቶች ተጠቃሚነት ላይ የታዩ ውስንነቶችን በመለየት በልዩ ትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል።

በአሉታዊ መጤ ልማዶች ወጣቱ ሰለባ እንዳይሆን ትኩረት ያሻዋል ያሉት ወ/ሮ እመቤት ወጣቶች የተለያዩ ኢንተርፕራይዞች ላይ ተደራጅተው እንዲሰሩ በቢሮው የግንዛቤ መፍጠር ስራ በቀጣይ ሊጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ዘጋቢ: ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን