በትራንስፖርትና መንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ ዉጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠልና በአፈጻጸም ሂደት ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ጉድለቶችን ፈጥኖ በማረም ለተሻለ ስኬት እንደሚሰራ ተጠቆመ  

ሀዋሳ፡ ጥር 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በትራንስፖርትና መንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ ዉጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠልና በአፈጻጸም ሂደት ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ጉድለቶችን ፈጥኖ በማረም ለተሻለ ስኬት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ  ልማት መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያዉ በ2016 በጀት አመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት ተቋማዊ የምክክር ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

“በመንገድ ግንባታ የባለሃብትና የማህበረሰቡን ተሳትፎ በዘላቂነት እናረጋግጣለን” በሚሉና በሌሎችም መሪ ሀሳቦች በተጀመረው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙራድ ከድር ተቋሙ በተሰጠው ግዙፍ ተልዕኮ ልክ ከፍተኛ አመራሩ ትርጉም ሰጥቶ ከማገዝና ከመደገፍ አኳያ ክፍተት ያለበት ነዉ ብለዋል።

የተቀናጀ፣ ፍትሃዊና ከአደጋ የፀዳ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳለጥ የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሙራድ በባለፈው 2015 በጀት አመት ከ89 ሚሊየን ብር በላይ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ትላልቅ ድልድዮች መገንባት መቻሉንም አብራርተዋል።

በመድረኩ የ2016 በጀት አመት በባለፉት 6 ወራት የተከናወኑ ጠንካራና ደካማ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በመምሪያው ምክትልና ሁሉ አቀፍ ገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ዘርፍ ሀላፊ በወ/ሮ መቅደስ ሳህሉ እና የትራንስፖርት ዘርፍ ሀላፊ በአቶ ግሩም ወ/ሰንበት ቀርቦ ሰፊ ዉይይት ተደረጎበታል።

ከዉይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ትግስቱ ተኸልቁ እና የቸሀ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ጌቱ አድማሱ እንዲሁም የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ገና ደገሙ ይገኙበታል።

ከየአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተደምሮ በተለይም የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተስተዋሉ  ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተደራጀና የተቀናጀ የቁጥጥር ስርዓትና እርምጃ የመዉሰዱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በሰብአዊና ቁሳዊ ሀብቶች ላይ ዉድመት እያስከተለ ያለዉን የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በባለፉት አመታት በህዝብ ንቅናቄ የመጡ ለዉጦች መኖራቸውን የተናገሩት ሀላፊዎቹ ይህንን ተግባር በማጠናከር የመንገድ ደህንነት የማረጋገጥ፣ ክትትልና ግንዛቤ የማሳደግ ስራ ቀዳሚ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

በቀጣይ በዘርፉ የተሰሩ መልካም ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠልና ድክመቶችን በማረም በተቀናጀ መልኩ   እንደሚሰራም የዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙራድ ከድር ተናግረዋል።

በመድረኩ ከጉራጌ ዞን ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የዘርፉ የስራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ብርሀኑ ማሞ – ከወልቂጤ ጣቢያችን