አልሚ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ የወሰዱትን መሬት ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ቢያስገቡ ከአካባቢ ተጠቃሚነት ባለፈ እንደሀገር ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም የሚቻል ሆኖ ሳለ በአንፃሩ በዘርፉ ሰፊ ውስንነት እንዳለ ተመላከተ

ሀዋሳ፡ ጥር 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) አልሚ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ የወሰዱትን መሬት ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ቢያስገቡ ከአካባቢ ተጠቃሚነት ባለፈ እንደሀገር ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም የሚቻል ሆኖ ሳለ በአንፃሩ በዘርፉ ሰፊ ውስንነት እንዳለ ተመላክቷል።

በአሪ ዞን ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

በዞኑ 11 በመንግሥት በኩል ምን ያህል መልማት የሚችል የመሬት አቅም እንዳለ በመረጃ አስደግፎ አለመለየት፣ የማስተዋወቅ ውስንነት፣ ድጋፍና ክትትል ሥራ አለመኖር፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን አለመሟላት የሚሉና ሌሎችም ችግሮች ተነስተዋል።

በሌላ በኩል አልሚ ባለሀብቱ የሚፈለገውን ሥራ በአግባቡ እንዳይሠራ በተለያየ ጊዜ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግርች እንደማነቆ ሆኖ በአሪ ዞን ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ልማት መመሪያ ሀላፊ አቶ ፍቅረስላሴ ጀማል አብራተዋል።

ከባለሀብቱ በኩል ደግሞ መሬቱን ተረክቦ በዕቅድ አለመመራት፣ ግብር አለመክፈል፣ የተረከቡትን መሬት አጥሮ ከማስቀመጥ አሊያም ጥቂት የመሬት መጠን እያለሙ ለረጅም ጊዜ መቆየት፣ለማልማት ውል ከተገባው ዘርፍ ውጭ ሌላ ተግባር ላይ መሠማራት፣ ከባንክ የተበደሩትን ገንዘብ በወቅቱ ምላሽ አለማድረግ ክፍተቶች መኖሩም በመምሪያ ሀላፊ በኩል ቀርቧል።

በቀጣይ ከላይ ከመንግስትና ከአልሚ ባለሀብቶች በኩል የተለዩ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ተፈቶ ወቅቱን የጠበቀ ልማት በሁሉም ባለሀብቶች ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት በአቶ ፍቅረስላሴ በኩል እንደመፍትሄ አማራጭ ሆኖ ተብራርቷል።

የፀጥታና መሰል ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች በመንግስት በኩል በልዩ ትኩረት መሰራት እንዳለበት ተገልጿል።

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሀም አታ እንደገለፁት በዞኑ አልሚ ባለሀብቶች በስፋት መጥተው እንዲያለሙ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ከዚህ በፊት መሬት ተረክበው ያላለሙ ባለለብቶች ችግራቸውን ፈትተው በሙሉ አቅም ወደ ተግባር እንዲገቡም አቶ አብርሃም አሳስበው በዘርፉ ያሉ የመሠረተ ልማትና ፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት የዞኑ አስተዳደር እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

የደቡብ አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለዮ ለባሽ በዞኑ ዘርፍ ሰፊውን ድርሻ በደቡብ አሪ ወረዳ እንደሚገኝ ገልፀው በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታት በጋራ ቅንጅት ለተሻለ ለውጥ ይሠራል ብለዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ አልሚ አዲስና ነባር ባለሀብቶች በራሳቸው ያለባቸውን ድክመቶችን ጠቅሰው እንደሚያርሙ ገልፀው በመንግስት መመቻቸት ያሉባቸው ጉዳዮች እንደሚመቻችላቸው ጠይቀዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን